ኢህአዴግ “አልመረመርም፣ አልበረበርም” በማለት ሲያንገራግር ከቆየ በኋላ በዓለም ባንክ ቀጭን ትዕዛዝ ለመበርበር መስማማቱን ገልጾ በተለያዩ አካላት ምርመራ ተካሂዶበታል። በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው ምርመራ አካል የሆነው የመጨረሻ ምርመራ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ተጠናቋል… የጎልጉል ታማኝ ምንጮች እንደተናገሩት ስድስት አባላትን ያካተተው የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን ኢህአዴግን መርምሮ ተመልሷል። የሚጠበቀው የመጨረሻው ሪፖርትና ሪፖርቱ የሚቀርብለት የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ነው። በቅርቡ የሚወጣውን ውሳኔ አቅጣጫ ለማስቀየር በማሰብ ኢህአዴግ ለመርማሪው ቡድን ራሱ የፈጠረውን “የተጭበረበረ ሪፖርት” አቅርቦ ነበር፡፡
ኢህአዴግ ምርመራውን በተቀነባበረ የፈጠራ ሪፖርት ለማምለጥ ሞክሮ እንደነበር የጠቆሙት የመረጃው ምንጮች “የመርማሪዎቹ ቡድን ሪፖርቱን አንቀበልም፣ የችግሩ ሰለባዎችና ክሱን የመሰረቱት ክፍሎች በሚኖሩበት ቦታ በመገኘት ነዋሪዎችን በተናጠል ለማነጋገር እንፈልጋለን” በማለት ኢህአዴግን እንደሞገቱት አስታውቀዋል። ኢህአዴግ በልማትና በህዝብ ስም የሚያገኘውን ከፍተኛ የዕርዳታ ገንዘብ የጦር ሃይሉን ለማደራጀት፣ የደህንነትና የፖሊስ ሃይሉን ለማስታጠቅና ርዳታ በሚለመንባቸው ዜጎች ላይ የተለያየ ወንጀል ፈጽሟል፣ አሁንም እየፈጸመ ነው በሚል መወንጀሉ ይታወሳል።
የምርመራው መነሻ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በቀድሞው ጠ/ሚኒስትርና የጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ፣ የህወሃትና የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝና በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች በጋምቤላ ክልል የተከናወነው የጅምላ ጭፋጨፋ ነው። በወቅቱ የተካሄደው ጭፋጨፋ ከ400 በላይ የተማሩ የአኙዋክ ወንዶች ላይ ያተኮረ እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ዓለም አቀፋዊ ሪፖርቶችና የጉዳዩ ሰላባዎች ይፋ ያደረጉት ጉዳይ ነው። አቶ መለስ ሞት ቀደማቸው እንጂ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቀረበባቸውን የክስ ማስረጃ ተቀብሎ ክስ እንዲመሰረትባቸው ከድምዳሜ መድረሱም ይፋ ሆኖ ነበር። ኢህአዴግ በዚሁ ፍርድ ቤት ላይ የአፍሪካ መሪዎችን የማስተባባርና የፍርድ ቤቱን አካሄድ ማውገዝ የጀመረው አቶ ኦባንግ የሚመሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ አቶ መለስ ላይ የመሰረተው ክስ እንዲከፈት መወሰኑን ተከትሎ እንደሆነ በወቅቱ ከየአቅጣጫው አስተያየት የተሰጠበት ጉዳይ ነው።
ከዚህ “ዘግናኝ” እንደሆነ ከሚነገርለት ጭፍጨፋ በኋላም በጋምቤላ ሰፋፊ ለም መሬትን በኢንቨስትመንት ስም ነዋሪዎችን በሃይል እያፈናቀለ በመሸጡ ኢህአዴግ ይከሳሳል። በተለይም የኦክላንድ ተቋምና (Oakland Institute) ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት (Human Rights Watch) ያቀረቡዋቸው ሪፖርቶች ኢህአዴግ በስድብና “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ ተጻራሪዎች፣ ርዕዮተ ዓለሙ ላይ የተነሱ፣ አይኗ እየበራ ያለችውን ኢትዮጵያን ለማጥፋትና ወደኋላ ለመጎተት ልዩ ተልዕኮ ያላቸው፣ የነፍጠኛውን ስርዓት መልሶ ለመትከል የሚሰሩ፣ ጸረ ልማቶች፣ ወዘተ” በማለት ቢያጣጥላቸውም ቀን ጠብቀው ስራቸውን እየሰሩ ስለመሆናቸው እየተነገረ ነው።
