ከሉላዊ ሴራ – የተሸሸጉ ታሪኮች the first blog in Amharic የተወሰደ ነው::
ጋርዮሻዊነት የተባለው ከጥንት ሲንከባለል የመጣና ከሰው ተፈጥሮ የማይታረቅ በመሆኑ ተቀባይ ያጣ፣ ግለሰቡን ከነጻነት አምዶች አንድ የሆነውን ንብረት የማፍራትና የመያዝ መብቱን እና ሌሎችም ሰብአዊ መብቱን ከላይ በእቅድ…. በሚመሩቱ ብቻ በሞኖፖል መያዝ አለበት የሚል ዘመናዊ ስሙ ኮሚዩኒዝም የተባለ ፍስፍና ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በውጭም በሃገራችንም “ኮሚኒዝም ይመጣል” የሚል መልእክት ከወቅቱ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ጋር በማያያዝ የሞተው ትንቢትን ዳግም እያስተጋቡ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ሳነብ ሁሌም፡- “ከዚህ ቀደም በመላው ዓለም በተግባር ተፈትሾ አውዳሚነቱን አስመስክሮ የከሸፈው ኮሚኒዝም ተመልሶ ገና ወደፊት እንዳይመጣ እንደማስጠንቀቅ ምነው ያሟርታሉ፡፡” እላለው፡፡ ጽሑፋቸውን ሳነበው “ካፒታሊዝም አበቃለት፣ ሰርቶ-አደሩ ኮሚኒዝምን ሊቀበል ነው፡፡” የሚል ሐሳባቸውን ያለ በቂ ትንተና ስሜት ቀስቃሽ አድርገው ይጽፋሉ፡፡
በጽሁፋቸው መሰረት ካፒታሊስቶች በቃኝ ስለማያውቁ ትርፋቸውን ለማብዛት ሲሉ አብዝተው በማምረት በተረፈ ምርቶቻቸው ዓለም ከተጥለቀለቀች በኋላ ቀውስ ይከተላል፣ ይህን ለመታደግም ካፒታሊስቶቹ ኢምፐርያሊስት ፖሊሲ በማራመድ የድሃውን አገር ጥሬ ሃብትና ገበያ ይበዘብዛሉ፣ መጨረሻ ላይ የሰርቶ-አደሩ ንቃተ ሕሊና ሲዳብር ሶሻሊስት (ሕብረተሰባዊ) አብዮት ይከተላል ይህም በኮሚኒዝም (ጋርዮሻዊነት) ይገባደዳል ይላሉ፡፡
ይህ ነገር ይሆናል የተባለው አሁን የገጠመው ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ተከትሎ ሳይሆን ቀድሞ ማርክስ ይሆናል ብሎ ተንብዮ ከከሸፉት ውስጥ ያለ ንድፈ ሃሳብ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ጽሑፍ 2 እንዲህ ያለው ሃሳብን በዝርዝር መረጃዎች ላይ ተመርኩዘን ለቀውሱ ትክክለኛ ምክንያት በመዳሰስ በርእዮተ ዓለማዊ እምነት ሳንታወር እውነቱን እናያለን፡፡ ከላይ ያስቀመጥነው የማርክስ ጥቅስ በ19ኛው ክ/ዘመን ሙታንን ለመቅበር ሲታክት የነበረውን ሊያሳይ ያለው ሲሆን ዛሬ ደግሞ ይህ ጥቅስ እራሱ በሚገርም መልኩ፣ ሃሳቦቹ በተግባር ተሞክረው ያለፈ ትውልድ ሙታን ልምድ ሁነው አሁን በተራቸው ምድርን እያስጨነቋት ይገኛሉ፡፡
ማርክስ ምን አለ?
ማርክሳዊ ትንታኔ ቁሳዊ ሁናቴዎችን በመተንተን ይጀምራል፡፡ የማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀሩ ወይም የአመራረት ዘይቤው ሌሎች ማህበራዊ ሁናቴዎች የታነጹበት መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሌሎች ማህበራዊ ሁናቴዎች የሚባሉት እንደ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ስርዓቶች፣ ስነ ምግባር እና ርእዮተ ዓለም ወዘተ. ሲሆኑ ላእላይ-ቅርጽ ይባላሉ፣ ለነዚህ ኢከኮኖሚያዊው ስርአት መሰረት ይሆናቸዋል፡፡ የምርት ኃይሎች በተለይ ቴክኖሎጂ በተሻሻለ ቁጥር ማህበራዊ አወቃቀሩ ካልተቀየረ እድገትን አንቆ ይይዛል፡፡
ይህ ማነቆ እራሱን በማህበራዊ ግጭት አድርጎ ይገልጻል፣ ይህም በመደቦች መሃከል በሚደረገው ትግል የሚታይ ነው፡፡ በካፒታሊስት የአመራረት ዘይቤ ይህ ግጭት የማምረቻ መሳርያውን በተቆጣጠሩ በአናሳዎቹ (ብርዡዋ)እና ምርት እና አገልግሎቱን በሚሰሩ በብዙሃኑ (ሰርቶ አደሮች) መሃከል የሚደረግ ይሆናል፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ካፒታሊዝም ሰርቶ አደሩን የሚጨቁን ሲሆን ይህ ደግሞ ወደ ሰርቶ አደሩ አብዮት እንዲሄዱ ያደርጋል ይላል፡፡
የዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰሩት የሆኑትን ነጥቦች ዝርዝርን አንድ በአንድ እንመልከታለን፣ እኚህ ሃሳቦች ሁሉም በተግባርም በንድፈ ሃሳብም ስህተት መሆናቸው ታይቷል ሆኖም ግን ነገርን ከስሩ … እንደሚባለው በቅድሚያ ለብቻ ልንመለከታቸው ይገባል፡-
ማርክሲስታዊ ንድፈ ሃሳብ
ኢኮኖሚያዊ መሰረት
ከላይ እንዳየነው ማርክስ የአመራረት ዘይቤው ለማህበረሰቡ ከሌሎች ነገሮች በላይ ዋናው መሰረቱ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በዚህም ምክንያት ማርክስ“ቁሳዊ” ነው ይባላል፡፡ ማርክስ የሄግል ተማሪ እያለ የታሪክ ወሳኝ አምድ ሃሳብ (አይዲያ) እንደሆነ የተማረውን አልተቀበለም፡፡ የበላይ የሆኑ ሃሳቦች የቁሳዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውጤቶች ናቸው በማለት ሃሳብ ብቻ ማህበረሰቡን ሊቀይር ይችላል የሚለውን ተቃወመ፡፡
አምራች ኃይል እና አመራረት ዘይቤ
በአምራች ኃይል እና በአመራረት ዘይቤ ማሃከል ያለው መስተጋብር ምን አይነት ሕብረተሰብ እንደሚኖርና ምን አይነት ማህበራዊ ለውጥ እንደሚመጣ ወሳኙ ግብአት አድርጎ ይቆጥራል፡፡ አምራች ኃይል የባርያ ጉልበት፣ የማሽን ቴክኖሎጂ ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ የአመራረት ዘይቤ ደግሞ አምራች ኃይሉ በማን ባለቤትነትና ቁጥጥር ስር መሆኑን የሚገለጽበት ነው፡፡ በባርያ ስርአት ጌቶች ባሮችን አስገድደው ያሰራሉ፣ በፊውዳል (ባላባታዊ) ስርአት ጭሰኞች በባላባቶች ስር ናቸው፡፡ በካፒታሊስታዊ ህብረተሰብ ካፒታሊስቶች የማምረቻ ምንጮችን በመቆጣጠር በደሞዝ ሰራተኞች ቀጥረው ያሰራሉ፣ ትርፍ እናገኛለን ብለው ካመኑ፡፡
ሲጀምር መጀመርያ ላይ አዲስ አምራች ኃይሎችና አዲስ የአመራረት ዘይቤ ለሕብረተሰቡ የሚጠቅም ወይም ተራማጅ ነው፡፡ ግዜ እየገፋ ሲሄድ ግን ጥቅሙ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ አዲሱ ማሕበረሰባዊ የአመራረት ዘይቤ የአዲሶቹን አምራች ኃይሎች ሙሉ እድገትን መግታት ይጀምራል፡፡ ለምሳሌ ፊውዳሊዝም ወደ መጨረሻው ሲደርስ ሰራተኞች በነጻነት ለፈለጉት ሰው መስራታቸውን መፍቀድና መሬት መሸጥ ባላባቶችን የሚጠቅም ነገር አልነበረም፡፡ እኚህ ተግባሮች ይከለከሉ የነበሩ ቢሆንም በኋላ ላይ የካፒታሊስት አመራረት ዘይቤ አካል ሁነዋል፣ ይህም ካፒታሊዝም ላስገኘው የምርት እና ጥቅም እድገት ጠቅሟል፡፡ በዞህ መሰረት አሁን ደግሞ ዛሬ ላይ በካፒታሊስት ምርት ዘይቤ ምክንያት ረዥም እድሜ ያላቸው ምርቶችና፣ የተራቡትን ማብላት ወዘተ. የሚቻል አልሆነም፡፡ እኚህን ማህበራዊ ትርፍ ያላቸውን ነገሮች ማድረግ የካፒታሊስቶቹን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡
ስለዚህም በማርክስ ንድፈ ሃሳብ በአምራች ኃይሎች እና በማሕበረሰባዊ አመራረት ዘይቤ መሃከል ያለው መስተጋብርና የሚያስከትለው ውጤት የማሕበራዊ ለውጥ ቀዳሚ መንስኤ ነው፡፡
መደብ እና የመደብ ግጭት
የማሕበራዊ አመራረት ዘይቤ የተለያዩ መደቦችን ያሳተፈ ነው፡፡ መደብ የሚወሰነው ግለሰቡ ከማምረቻ መሳርያዎች ጋር ባለው ግንኙነት ነው፡፡ ለምሳሌ በመጨረሻው የካፒታሊስት ማሕበረሰብ ሁለት መሰረታዊ መደቦች ይኖራሉ፡ የማምረቻ መሳርያዎች ባለቤቶች ማለትም ካፒታሊስቶች እና የጉልበታቸው ብቻ ባለቤት የሆኑት ማለትም ሰርቶ አደሮች፡፡
ስለዚህ በየትኛውም የታሪክ ዘመን የበላይ እና አገልጋይ የሆኑ መደቦችን ማግኘት እንችላለን፡፡ ለማርክስ ሃብት ክፍፍልና ስልጣን ዋናው የስነ ምግባር (ሞራል) ጥያቄው ነበር፡፡ የማርክስ የመጨረሻ ህልሙ መደብ አልባ ሕብረተሰብ ነው፡፡ ለማርክስ ታሪክ ማለት የመደቦች የግጭት ታሪክ ማለት ነው፡፡ ማርክሲስታውያን ሁሌም የሚይቁት ጥያቄ የትኛው መደብ የበላይ ሆነ የሚለውን ነው፡፡ በካፒታሊስት ማሕበረሰብ ካፒታሊስቱ ይጠቀማል፡፡
ታሪክ
እስካሁን ካየነው ማርክስ የታሪክ ምልከታ ንድፈ ሃሳብ እንዳቀረበ መገመት ይቻላል፡፡ በዚህ ሃሳቡ መሰረታዊው ጭብጥ የሄግሊያዊ የሆነው “ዲያለክቲካል ሂደት” ነው፡ መጀመርያ አንድ ሃሳብ ወይም ሁኔታ – ተሲስ ይኖራል፤ ቀጥሎ የዚህ ተቃራኒ – አንቲተሲስ ይነሳል፤ የሁለቱ ግጭት ውህደታቸውን – ሲንተሲስ ይፈጥራሉ፤ ይህ ሲንተሲስ ደግሞ አሁን በተራው ተሲስ ይሆናል …፡፡ ለምሳሌ በታሪክ ባላባታዊ ስርዓቱ በውስጡ ተቃራኒ መደቦችን ይዞ ነበር፣ የበላይ የነበሩት የመሬት ባለ ቤት ባላባቶችና አዲስ ተነሱት ነጋዴዎች መደብ፤ እነዚህ ሁለቱ ሲጋጩ ውህደታቸው የሆነውን የካፒታሊስት ዘመን አመጡ፡፡
ስለዚህም ታሪክ መቀዳሚነት የቁሳዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ሁናቴዎች መገለጫ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ታሪካዊ ቁሳዊነት” እና “ዲያለክቲካል ቁሳዊነት”በመባል ሃሳቡ የሚጠራው፡፡ የማምረቻ ቴክኖሎጂ ደረጃ/ ዓይነት እና የነዚህ ቁጥጥርና ማህበራዊ ግንኙነት ነው የአንድ ሕብረተሰብ አደረጃጀትን ምንነት ማለትም ጥንታዊ (ጋርዮሽ)፣ ባርያ፣ ፊውዳል (ባላባታዊ) እና ካፖታሊስት መሆኑን እና ከአንዱ ወደ ሌላው መሸጋገሩን የሚወስነው፡፡ ማርክስ ይህ የታሪክ እይታው እንደ ዋና ግኝቱ ይቆጥው ነበር፡፡ ይህም እይታው ከዋጋ ንድፈ ሃሳቡ ጋር በጋራ ነበር ማርክሲስታዊነትን እንደ ሳይንስ ያስቆጠሩት፡፡ (ለነዚህ የተሰጠውን ምላሽ እንደርስበታለን፡፡)
ይህ የግጭት ዲያለክቲክ ሂደት ግን መጨረሻ አለው፡፡ ተሲስ የሆነው ካፒታሊዝም እና አንቲተሲስ የሆነው ሰርቶ አደር ወደ ውህደት የሚመጡ ሲሆን የዛኔም መደብ አልባ ሕብረተሰብ ይገኛል፡፡ የለውጥ ምንጩ የመደብ ልዩነት እንደመሆኑ መደብ አልባ ማሕበረሰብ ሲመጣ ዲያለክቲካል ሂደቱ መጨረሻው ይሆናል፣ ከዚህም በኋላ ፖለቲካዊ ለውጥ አይኖርም፡፡
የካፒታሊስት ምርት ዘይቤ
በካፒታሊስት ማሕበረሰብ የሚገኙት የምርት ኃይሎች የፋብሪካ ዘዴዎች (ቀድሞ በቤት በግል ይመረት ከነበረው በተለየ መልኩ) እና የከባድ ማሽን ቴክኖሎጂ ዘዴን ያካትታል፡፡ ይህ ዘይቤ ሰፊ የካፒታል ሃብት ማፍሰስን ይጠይቃል፡፡ እዚሕ ያለው ማህበራዊ ግንኙነት የማምረቻ መሳርያውን በያዙት ወይም በሚቆጣጠሩትና ትርፍ በሚገኝበት ብቻ የሚያውሉት ጥቂቶቹ ካፒታሊስቶች እና በሥራ ቦታ ምንም ድምጽ የሌላቸው ጉልበታቸውን ለካፒታሊቶቹ የሚሸጡ ብዙሃን ሰርቶ አደሮች መሃከል ያለው ነው፡፡
ማርክሲስታውያን ሥራ ብቻ ነው ገንዘብ ማስገኘት ያለበት እንጂ ገንዘብ፣ ገንዘብ ማስገኘት የለበትም ይላሉ፡፡ ማለትም ሃብታሞች ባስቀመጡት ገንዘብ ወለድ ወይም ባፈሰሱት ሃብት (ኢንቨስትመንት) ገቢ ማግኘት የለባቸውም ይላሉ፣ በተለይም ይህ አንድ ሰው ሃብታም በሆነ ቁጥር ስራ ሳይሰራ ይበልጥ ገቢ እንዲያገኝ የሚያደርገው እንደመሆኑ … ሃብታሞች ገቢያቸውን ተጠቅመው፣ ለማግኘት መስራት ያለባቸው ሰዎች ያመረቱት ምርት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡
ትርፍ እና ፍላጎት
ሌላው የኢኮኖሚክስ አስተምህሮ ምርት እና እድገት በትርፍ መመራቱ ጥሩ ነው ይላል፡፡ ይህ የሚባለው ካፒታሊስቶች ሰው የሚፈልገውን ምርት ሲያመርቱ ትርፋቸውን ያሳድጋሉ፣ በዚህም አዋጭ የሃብት አጠቃቀም ይፈጠራል ከሚለው እሳቤ ነው፡፡ ማርክሲስታውያን ግን ለትርፍ በሚደረግ ምርት እና ፍላጎትን ለማሟላት በሚደረግ ምርት መሃከል ሰፊ ልዩነት አለው ይላሉ፡፡ ይህ ሃሳብ ጥሩ ቢሆንም ለመተግበር ሲሞከር ትርፍን አማክለው ከሚሰሩት የባሰ ጥፋት ይከተላል፣ ተግባራዊም አይደለም፡፡ (እንመለስበታለን፡፡)
የሰራተኛ ዋጋ ንድፈ ሃሳብ
ማርክሲስቶች የምርቶች ዋጋ ለማምረት በፈጀው ሰራተኛ (ኃይል) ነው መሰላት ያለበት ይላሉ፡፡ ሌላው ይህን የሚወስነው ገበያው እንዳቀረበለት ነው፡፡
ትርፍ እና ብዝበዛ
የማርክሲስታዊነት ዋናው አምድ በካፒታሊስቶች ያለው የትርፍ ማግኘት ዘዴ የሰራተኞች ብዝበዛ ነው የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ ካፒታሊስቱ ለሰራተኛውና ሌሎች ግብአቶች ያወጣውን ጨምሮ ምርቱን በትርፍ ሲሸጥ ሰራተኛው የፈጠረውን እሴት እየወሰደ ነው፡፡ በመሸጫ ዋጋው ላይ የታየው የሰራተኛው ሥራ የፈጠረው ነው፣ ሆኖም ግን ሰራተኛው የተቀበለው ከዚህ የሚያንስ ነው፣ ስለዚህም ካፒታሊስቱ እየበዘበዘው ነው፣ ምርት ማምረቱ ላይ በስራ ሳይሳተፍ የምርት ሁናቴ ተቆጣጣሪ በመሆኑ ምክንያት ይላሉ፡፡
የካፒታሊዝም መጣረስ
ማርክስ በመጀመርያ ላይ ካፒታሊዝም ተራማጅ እድገቶችን ያስመዘግባል፣ በተለይ በምርት መጨመርና ከዚህም በሕብረተሰቡ ቁሳዊ ሐብት መካበት ያስገኛል ይላል፡፡ ግዜ በሄደ ቁጥር የምርት ኃይሎች እና የማሕበራዊ ምርት ዘይቤ ወደ ግጭት ይገባሉ፣ እናም ማሕበራዊ የምርት ግንኙነቶች የቴክኖሎጂና የምርታማነት ሙሉ አቅሞችን ለማሕበራዊ ፋይዳ እንዳይውል ያደርጋል፡፡ እኚህ ውስጣዊ ግጭቶች እየከረሩ ሂደው ከግዜ ሒደት በኋላ የካፒታሊስታዊ ስርዓትን ያጠፉታል፡፡
በካፒታሊዝም ስርአት ውስጥ እራሱን እንዲያጠፋ የሚያደርገው ስርአቱ የቆመበት ካፒታሊስቶቹ ትርፍ የሚያከማቹበት ሒደት ነው፡፡ ካፒታሊስቶች እርስ በእርስ ይፎካከራሉ፣ ሁሌም አዋጭ አመራረት ዘዴ እና የተሻለ ቴክኖሎጂ ለማግኘት ይፋካከራሉ፡፡ ይህም ካፒታሊስቶቹ ሃብታቸውን ይበልጥ ወደ ማሽን (ቋሚ ካፒታል) እንዲያፈሱ እና ሰራተኛ ለመግዛት የሚያወጡትን እንዲቀንሱ ያደርጋል፡፡ ይህን ይበልጥ ለካፒታል ወጪ መብዛቱና ለሰራተኛው መቀነሱን ማርክስ የካፒታል “ተፈጥሯዊ ውህደት” / “organic composition” ይለዋል፡፡ በዚህ የካፒታል ሂደት ምክንያት የሰራተኛው ስቃይ እየባሰ ይሄዳል፣ የካፒታሊስቱ ሃብት እየጨመረ ሲሄድ፡፡ በዚህ የሰራተኞቹ መዳከም ምክንያት የካፒታሊስቶቹን ምርት የሚገዛ ስለማይኖር በረዥም ግዜ ሂደት የካፒታሊስት ትርፎች እየቀነሱ ይሄዳሉ፡፡ በካፒታሊዝም ውስጥ የተገነቡት እኚህ ተፈጥሮው ምክንያት በግዜ ሂደት ካፒታሊዝም ይከስማል፡፡ አብዮት እንዲነሳ በሚያደርግ ደረጃ የካፒታሊስቱ ትርፍና የሰርቶ አደሩ ሕይወት ደረጃ ይወርዳሉ፡፡
ማከማቸት
ማርክሲስቶች በካፒታሊስት ማሕበረሰብ የሚገፋው ሃይል ማለቅያ የሌለው ትርፍ የማከማቸት ሩጫ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ለለውጥና ፈጠራ ይመቻል፡፡ ካፒታሊስቱ የውድድሩ እስረኛ ነው ወደ ኋላ ከቀረ ይጠፋል፡፡ ይህ ገዳይ ፍክክር ደግሞ ማርክሲስቶች አይወዱትም፡፡
የትርፍ ምርት ችግር
ካፒታሊዝም ሁሌም እየተከማቸ ላለው ካፒታል ትርፋማ የማድረግ ፈተና አለበት፡፡ የትርፍ ምርት ችግር ወደ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) እንዲኬድ ያደረገው ዋናው ምክንያት ነው፣ ምክንያቱም ሉላዊነት ትርፋማ መስኮች ላይ ሃብታቸውን የሚያፈሱበት አዳዲስ በሮች ይከፍትላቸዋልና፡፡
የተነጠለ ሰራተኛ
ካፒታሊዝምን ከወቀሰበት ሌላው ብዝበዛ ሰራተኛው እንዲነጠል ያደርገዋል የሚል ነው፡፡ ለአዋጭ ምርታማነት ሲባል ሰራተኛው በአንዲት ሙያና ተደጋጋሚ ተግባር ያለው ሥራ ላይ እንዲያተኩር ስለሚደረግ፣ የሥራውን የመጨረሻ ውጤት አያዩም፣ ሥራ ይታክታል፣ ምርቱም የሰራተኛው ስላልሆነ ምን መሆን እንደሚገባው መወሰን አይችሉም፣ የመሣሪያዎቹ ባለቤት አይደሉም፣ በሥራ እቅድና አደረጃጀት ድምጽ የላቸውም፣ የተባሉትን ብቻ ይሰራሉ፣ መመሪያዎችን መጣስ የለባቸውም በተለይ ሰዓት በሚመለከት፣ ይህ በሰፊ የሥራ ክፍፍል ውስጥ ሁነው ይሸከሙታል፡፡ የግል መነሳሳታቸውን ለመፈጸም እድል የላቸውም፡፡ በስራው ሂደት ያላቸው ብቸኛው ግንኙነት የሚቀበሉት ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ (እኚህ ሁኔታዎች ማርክስ በነበረበት ግዜ የነበሩ የፋብሪካ ሰራተኞችን እንጂ የዘመናዊውን የቢሮ ሰራተኞች አይገልጽም)
ማርክስ የሚያረካ ስራ የሰው ልጆች ስሜታዊና መንፈሳዊ ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ይሰጠዋል፡፡ ካፒታሊዝም ሰራተኞች የሚያስደስታቸው እና ማሕበረሰባቸውን የሚጠቅም ስራ ላይ እንዳይሰማሩ ያደርጋል ይላል፡፡ (በተግባር የሆነው ተቃራኒው ነው፡፡)
የማሕበረሰብ መውደም
ማርክስ ካፒታሊዝም ኢኮኖሚያዊ ወይም ትርፍ-ተኮር ያልሆኑ እሴቶችን በማጥፋት ገንዘብ ነክ በሆኑት ይተካቸዋል ይላል፡፡ ገበያ እና ካፒታሊስቶች በሚፈልጉት ተንቀሳቃሽ ሰው ሃይል ምክንያት ሰራተኞች ከቦታ፣ ቡድኖች፣ ሰዎችና ባህሎች ጋር ያላቸው ጠንካራ ስሜታዊ ግንኙነቶችን አጥፍቷል፣ ይህ ማሕበረሰባዊ ትስስር እንዲቀንስ አድርጓል ይላሉ ያሁኖቹ ማርክሲስቶች፡፡ አሁን ግለሰቡ ከማሕበረሰቡ ተነጥሎ ይኖራል ያለ ማሕበራዊ ግዴታና ትስስር፡፡ በዚህም ሳቢያ ጭንቀት፣ ብቸኝነት፣ ግለኝነትና የቤተሰብ መፍረስ፣ ራስን ማጥፋት፣ ወንጀል፣ ሱሰኝነት ወዘተ. ተከትሏል፡፡
በሌላ አገላለጽ ካፒታሊዝም ሁሉን ነገር ወደሚሸጥ ሸቀጥ ቀይሮታል፣ በተለይ ሥራን፡፡ ሥራ፣ መሬት እና ገንዘብ በፊውዳል ዘመን የሚሸጡ ሸቀጦች አልነበሩም፡፡
መንግስት
ማርክሲስታውያን መንግስት በማሕበረሰቡ የበላይ የሆነውን መደብ ያገለግላል ይላሉ፡፡ በካፒታሊስታዊ ማሕበረሰብ መንግስት የካፒታሊስት መደብን ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ መንግስት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን መጨመር ቅድሚያ የሚሰጠው ስራው ይሆናል፣ ይህ የኑሮ ጥራት መውረድና ስነ ከባቢያዊ ቀውስ ቢያስከትልም፡፡ የመንግስት ዋና ባሕርይ የሕብረተሰቡን አባሎች መስገደድ፣ መቅጣት እና ጦርነት መክፈት መቻሉ ነው፡፡ ይህን አቅሙን የሚጠቀምበት የበላይ የሆነውን መደብ ለመጥቀም ነው፡፡ መደብ አልባ ማሕበረሰብ ሲመጣ መንግስት አስፈላጊ አይሆንም፡፡
ርእዮተ ዓለም፡ የተሳሳተ ንቃተ ሕሊና
የሚበዘበዙ መደቦች ሁኔታቸውን ወይም የሚጠቅማቸውን ባግባቡ አይረዱም፡፡ ነባራዊው ሁናቴ ፍትሃዊ ነው ብለው እንዲቀበሉ ይደረጋሉ፡፡ ለምሳሌ በባላባታዊ አስተዳደር ንጉሱ እግዚአብሔር የሾመው ነው ብለው ያምናሉ፣ ምድራዊ ድህነታቸውም ወሳኝ እንዳልሆነና በቀጣይ ሕይወት ለመካስ ማሰብ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ በእኛ ዘመን ደግሞ ትላልቅ ሚድያዎች የበላይ የሆነውን ርእዮተ ዓለም ያሰርጻሉ ይላሉ ማርክሲስቶች፡፡
በየትኛውም መደባዊ ሕብረተሰብ የበላይ የሆነውን መደብ የሚመች ርእዮተ ዓለም ይኖራል፡፡ ሰራተኛው መደብ ለካፒታሊስቱ የሚመቹ እሴቶችን ሲቀበል “የቡርዥዋ የበላይነት” ይበላል፡፡ ማርክስ በካፒታሊዝም ማብቅያ ሰራተኞች ስለሁኔታቸውና ጥቅማቸው የበለጠ መረዳት ያዳብራሉ፣ የመደብ ንቃተ-ሕሊና ይመጣል፡፡
አብዮት
ማርክስ ካፒታሊዝም በውስጡ ያሉ ችግሮችን እስኪያጠፉት ድረስ የሚያደርሱ ኃይሎችና ሂደቶችን ይዟል ብሎ ያምናል፡፡ በምርት ኃይሎችና ዘይቤ መሃከል ያለው መስተጋብር እየተሸረሸረ ሲሄድ ግጭቶች እየባሱ ይመጣሉ፣ ካፒታሊስትና ሰርቶ አደር መደቦች መሃከል ያለው ልዩነት እየሰፋ፣ የሰርቶ አደሩ መከራ እየበዛ፣ የሰርቶ አደሩ ንቃተ ሕሊና ሲጨምር፣ መጨረሻ ላይ አብዮት ይፈነዳል፡፡
ከአብዮት በኋላ መጀመርያ የሰርቶ አደሩ አምባገነን መንግስት የሚመሰረት ሲሆን፣ ይህ የካፒታሊዝም ቅሪቶችን በተለይም የብርዥዋ ርእዮተ ኣለምን የሚያንጹት እሴቶችን ማጥፋት ላይ ይሰማራል፡፡ አምባገነናዊው መንግስት እየሳሳ ይሄዳል፣ ሰፊ የሥራ ክፍፍልና ሙያ ተኮርነት ይጠፋል፣ የግለሰቦች አመለካከት ማሕበራዊ ይሆናል፡፡
ማርክስ ምን ሳተ?
ማርክስ ምን እንደሚል በዝርዝር ማቅረብ ያስፈለገው አንድ ስለእርሱ ሂስ ስናቀርብ ስለምንናገረው እንደምናውቅ ለማሳየትና ሁለት አንባቢው ተጫዋቾቹን ሁሉንም በሚገባ እንዲረዳ በሚል ነው፡፡ ማርክስ ያቀረባቸው ሁሉ ትንተናዎች ስህተት ናቸው፡፡ ስህተት መሆናቸውን እናያለን፤ ቀጥለን ደግሞ እንዲህ ስህተት ከሆነ ሰዎችን ለምን ይስባል የሚለውን እናያለን፡፡
ኢኮኖሚያዊ ሂስ
ማርክሲስታዊ ኢኮኖሚክስ በካፒታሊዝም ትንታኔው ስህተት እና ማርክሲስታውያን በሚያቀርቡት መተግበር የማይቻል ኢኮኖሚያዊ ስርአት ላይ በመመርኮዝ ይተቻል፡፡
የሰራተኛ ዋጋ ንድፈ ሃሳብ
በሉድዊግ ቮን ሚዝስ የተመሰረተው የኦስትርያ ኢኮኖሚክስ አስተምህሮ የማርክስ ኢኮኖሚያዊ ስርአት በክላሲካል የሰራተኛ ዋጋ ንድፈ ሃሳብ ላይ በመመስረቱ ይወቅሰዋል፣ ምክንያቱም ንድፈ ሃሳቡ ስህተት ነውና፡፡ ይህ ንድፈ ሃሳብ የሚለው እንዳየነው የአንድ ምርት መለክያ መሆን ያለበት የፈሰሰበት የሰራተኛ ጉለበት ብቻ ነው፡፡ ይህ ቀድመውት በነበሩ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች እንደ አዳም ስሚዝ እና ዴቪድ ሪካርዶ ይጠቀሙበት የነበረ ነው፡፡
[3] ማርክስ ክላሲካሎቹ ትርፍን ሙሉ ለሙሉ ማብራራት እንዳልቻሉ የተናገረው ልክ ነው፣ ሆኖም ግን እርሱም ትርፍን በትክክል አላብራራም፡፡ ማርክስ ክላሲካሎቹ ሃሳቡን ማድረስ ከፈሩበት ቦታ አድርሶ የካፒታሊዝም በዝባዥነት ማሳያ ያደርገዋል፡፡ እንደማርክስ አባባል ዋጋ በሰራተኛ ጉልበት ብቻ መለካት ስላለበት ካፒታሊስቱ ገበያ ላይ ለጉልበት ካወጣው ዋጋ በላይ ሲሸጥ ያገኘው ትርፍ የብዝበዛ ውጤት ነው ይለዋል፡፡ ማርክስ የሰራተኛ የዋጋ ንድፈ ሃሳብን ለጥጦ ካፒታሊዝምን ለመውቀስ ሲጠቀምበት የራሱን አጠቃላይ ሃሳብ ድክመት ነበር ያሳየው፡፡
ከ19ኛው ክ/ዘመን ማገባደጃ ጀምሮ የሰራተኛ የዋጋ ንድፈ ሃሳብን የሚቀበል ቁም ነገረኛ ኢኮኖሚስት የለም፣ ከዚህ ይልቅ እንደ ኦስትርያ ኢኮኖሚክስ አስተምህሮ የምርት ዋጋ በሰው ምርጫ የሚወሰን በመሆኑ“እንደአመለካከት የዋጋ ንድፈ ሃሳብ” (subjective theory of value) ያራምዳል፡፡ የፈለገው ግብአት ቢጨመር ዋጋው በምርጫ ይገደባል የሚል ነው፡፡ ዛሬ ትርፍ ብዝበዛ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ ካፒታሊስቶች የዛሬ ፍጆታ ላይ ማዋል የሚችሉትን ገንዘብ ለፍጆታ ባለማዋል፣ የሚሆነውን በመቀበል ወይም ሪስክ በመውሰድ ገንዛብ በማፍሰስ፣ እና ምርት በማደራጀት የሚያገኙት ዋጋ ነው፡፡
የዋጋ አንቴናዋችን ማዛባት፡ የስሌት ችግር
ይህ የሶሻሊስት ኢኮኖሚ እቅድ አወጣጥን የሚወቀስበት ነጥብ ነው፡፡ መጀመርያ በሉድዊግ ቮን ሚዝስ በ1920 የተነሳ
[4] ሲሆን በኋላ በፍሬደሪክ ሃይክ
[5] ተብራርቷል፡፡ የተነሳው ችግር ግብአቶችን እንዴት በትክክል በኢኮኖሚው ውስጥ ማሰማራት ይቻላል የሚለው ነው፣ ምክንያቱም ያለ ዋጋ ፍላጎትን ማወቅ አይቻልምና፡፡ በነጻ ገበያ ውስጥ የዋጋ ስርአት ይፈታዋል፣ ሰዎች ሊከፍሉለት ዝግጁ የሆነ ነገር ግብአቱን ይጠቀምበታል፡፡ በግለሰቦች ደረጃ ዋጋ ለማውጣት በሚወስኑት ውሳኔ መሰረት እጥረት እና ተረፈ ምርት ክስተቶችን እንዲታረሙ ያደርጋል፡፡ ሚዝስ እና ሃይክ ይህ ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነና ያለዚህ ርቱእ በሆነ መንገድ ጥሬ ሃብት በቅጡ ማከፋፈል አይቻልም ይላሉ፡፡ ይህ የሶሻሊስት የታቀደ ኢኮኖሚ ሊሰራ እንደማይችል ማሳያ ነው፡፡ ክርክሩ በ1020ዎቹና 30ዎቹ የጦፈበት ዘመን ነበር፡፡
[6] በ1990ዎቹ በሶሻሊስት ኢኮኖሚዎች ክስመት ማን ልክ እንደነበር ታይቷል፡፡
ተነሳሽነትን ማኮላሸት
ሰርቶ አደሩ የማምረቻ መሳርያዎች ባለቤት ሲሆን ገቢውን ይከፋፈላል ይላል ማርክስ፣ ገቢ በግል የሚወሰን ካልሆነ የሥራ መነሳሳትን ያጠፋል፡፡
[7] ማንም የተሻለ ሥራ ቢሰራ የተሻለ ስለማያስገኝለት ለተሻለ ስራ የሚነሳሳበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ጆን ኬንዝ ጋልብረይዝ የተባለው ኢኮኖሚስት እንደሚከተለው ይላል፡
“ይህ ከማርክስ አልፎ ብዙዎችን ያዳረሰው [እኩልነትን መሰረት ያደረገ ማበረታቻ የላቀ ተነሳሽነት ያስገኛል] የሚለው ተስፋ፣ በታሪክና በልምድ ከንቱ መሆኑ ታጥቷል፡፡ ለበጎም ሆነ ለክፉ የሰው ልጆች ከዚህ የላቀ መዓረግ ደርሰው አያውቁም፡፡ የሶሻሊስ አመራር የተለያዩ ትውልዶች ይህን ሃቅ በውድቀታቸውና በሚያሳዝናቸው መልኩ ተምረውታል፡፡ መሰራታዊው እውነት ግልጽ ነው፡ መልካሙ ሕብረተሰብ ወንዶችና ሴቶችን ከነምንነታቸው ሊቀበል ይገባል፡፡”
[8]
ትርፍ እና ብዝበዛ
ማርክስ ካፒታሊዝም በብዝበዛ ላይ ተመሰረተ ስርዓት በመሆኑ እራሱን ማጥፋቱ አይቀርም የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ በአብዮት ተወግዶ በሶሻሊዝም ይተካል ብሎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው ከክላሲካል ኢኮኖሚስቶች የተዋሰው የተሳሳተ የዋጋ ንድፈ ሃሳብ ላይ ተሞርኩዞ ነበር፡፡ የሥራ ዋጋው ደሞዝ ሲሆን የካፒታል ዋጋው ደግሞ ትርፍ ነው፣ በሥራ ብቻ ያለካፒታል ምርቱ ስለማይገኝ የጋራ ዋጋ ነውና፡፡
ማርክስ በተጨማሪም ካፒታሊስቶች ትርፍ ማሳደድ ብቻ ስለሆነ ተግባራቸው፣ ይበልጥ ወጪ ለካፒታል እያወጡ ለሰራተኛው እየቀነሱ በሚሄዱበት ግዜ የሰራተኛው ኑሮ እየከፋ ሲሄድና፣ የካፒታሊስቶቹም ምርት የሚገዛ ሲጠፋ አብዮት ይነሳል ብሎ ገምቶ ነበር፡፡ በእውን የታየው ግን የቀዝቃዛው ጦርነት መጨረሻ የሆነው የሶሻሊስት ሃገሮች ኢኮኖሚ መክሰምና ከብረት መጋረጃው (አይረን ከርተይን) መፍረስ በኋላ እና እንደ ራሽያ እና ቻይና ሳይቀሩ ነጻ ገበያ ስርአት መቀበላቸውና (በቻይና ፖለቲካው ነጻ አልሆነም) ማርክሲስታዊ ስርአቶች መክሸፍ ተከትሎ ይህ ግምቱ ስህተት እንደሆነ ታይቶ ነበር፣ ዛሬ ላይ ግን ካፒታሊስቱ ዓለም ቀውስ ውስጥ ሲገባ ከዚህ ግምቱ ጋር የሚያገናኙት አሉ፡፡ ሆኖም ግን እንዲያውነም መንግስት ያለአግባብ ጣልቃ መግባቱ ነው (በሌላ አነጋገር ማርክሲስታውያን) ያመጡት ችግር ነው እንጂ ከካፒታሊዝም ጋር ግንኙነት እንደሌለው የሚያሳዩ ማስረጃዋች አሉ፣ እንመለስበታለን፡፡ ፍልስፍናዊ ትንታኔ ስላደረግነው ማርክሲስት ሳቦታጆችን አሁን አንጽፍም፡፡
አሁን የምናያቸው የኢኮኖሚ ከፍና ዝቅ ማለት ማርክስ እንዳለው የካፒታሊዝም መጣረስ ሳይሆን ከመንግስት የተሳሳተ ፖሊሲ የሚመነጭ ነው፡፡ ቮን ሚዝስ ነበር ለመጀመርያ ግዜ ሃሳቡን ያሳየው የቢዝነስ ኡደት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ የኡደቱ ምክንያትም የብድር ኡደት ነው፡፡ በኋላ ላይ ሃይክና ሌሎችም በስፋት አብራርተውታል፡፡ ይህ የሚከሰተው የገንዘብ አቅርቦቱን ለመጨመር በሚወሰዱ ፖሊሲዎች ሳቢያ ተገቢ ያልሆነ ኢንቨስትመንት እንዲደረግ ያደርጋል፡፡ ኢኮኖሚስቶች ንድፈ ሃሳቡ ልክ አይደለም ቢሉም ጄምስ ፒ. ኬለር በ2001
[9] እና ሮበርት ሙሊጋን በ2006
[10]ባደረጉት ጥናት ንድፈ ሃሳቡ ካለው የቁጥር መረጃ ጋር የሚገጥም መሆኑን አሳይተያዋል፡፡ ማእከላዊ ወይም ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ሕግ እና ደንብ አክብረው መንቀሳቀሳቸውን እንደማረጋገጥ ከዚህ ውጪ የሆነ ስራ ሰርተው ኪሳራ ሲደርስባቸው ይደጉማቸዋል፣ ችግሩ ከመቀረፍም እየከበደ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ ተጠያቂው ማእከላዊ ባንክና በገበያ ሕግ የማይገዛ የገንዘብ ፖሊሲ ናቸው፡፡
[11] ይሄ ሁሉ ስሕተት ማረም አቅቷቸው ሳይሆን ለፖለቲካዊ ግን ዓለምን አንድ አድርጎ ለመግዛት ስለሚፈልጉት ነው፡፡
ከዚህም ቀጥሎ ስለተነጠለ ሰራተኛ እና ሕብረተሰብ መውደም ያለውም ስህተት ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ሃሳቡ ወሳኝና ግን ደግሞ ጽኑ ባልሆነ መሰረት ላይ የቆመ ነው፡፡ እርሱም ሰዎች ገበያ መር የሆነ ውስብስብ ሕብረተሰባዊ ትስስርን አፍርሰው ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ የሆነ በእቅድ የሚመራ ሕብረተሰብ መተካት ይችላሉ በሚለው እምነቱ ነው፡፡ ማርክስ የሚለው የፉክክርና ትርፍ አሳዳጅ ማህበረሰብ በመሆናችን ብቻ አይደለም መነጠል የሚደርስብን፡፡ የሥራ ወይስ ደስታ ፍጥጫም አይደለም፡፡ ውድድር፣ ትርፍና ኪሳራ፣ ገንዘብ፣ የግል ንብረት ባለቤትነት ወዘተ. የሌለው ሙሉ በሙሉ በእቅድ እና ቁጥጥር የሚመራ ሕብረተሰብ ባለመፍጠራችን ነው ይላል፡፡ ከዚህ ከመነጠል ንድፈ ሃሳብ ጋር አንድ ችግር አለ፡ እንዲህ የተራቀቀ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ባለበት ዘመን እንኳ እጥረት እና ጥርጥርና የሚያስወግድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የእቅድ ስርዓት መፍጠር አልተቻለም፡፡ ካፒታሊዝም መነጠል ይፈጥራል ከተባለ ያለካፒታሊዝም ስኬታማ የሆነ በእቅድ የሚመራ ዓለም እውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ማርክስ በካፒታሊዝም የጋራ ዕጣ ፈንታችንን በእቅድ ከመወሰን ተነጥለናል ይላል፡፡ ሚዝስ እና ሃይክ እንዳሳዩን በእቅድ የተመራ ሕብረተሰብ መቅረጽና ስኬታማ መሆን የማይቻል ከሆነ እንግዲህ ከምንም ነገር አልተነጠልንም ማለት ነው፡፡
መንግስትን በተመለከተ የበላይ መደቦች መሳርያ ነው ያለውም ልክ አልሆነም፡፡ የነጻ ገበያ ባስገኘው ዲሞክራሲ የሚኖሩ ህዝቦች ከማንም በላይ መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው መንግስት እያስጠበቀላቸው ነው፡፡ አሁንም ይህን ለመቀልበስ የሚደረገውን ዓለም አቀፋዊ ሴራ አንዳስስም፣ ሆኖም ጨቋኝ ሁኖ የተገኙት እንዲያውም ማርክሲስት መንግስቶች ናቸው፡፡ የማርክሲስት መንግስቶች በዓለም ዙርያ መቶ ሚሊዮን ለሚሆን ሕይወት ሊያጠፉ ችለዋል፡፡
[12]
በነዚህ እስካሁን ባየናቸው ግምቶቹ መክሸፍ ምክንያት ይመጣል ያለው አብዮት አልመጣም፣ ይመጣል ያለባቸው በሰለጠኑት ወይም በኢንድስትሪ የበለጸጉ አገሮች ውስጥ ሳይሆን በይበልጥ ግብርና ውስጥ ባሉ እንደ ራሽያ፣ ቻይና፣ ሃገራችን ጨምሮ የአፍሪካ ሃገራትና ድሃ የምስራቅ አውሮፓና ላቲን አሜሪካ አገሮች ነው፡፡ በነዚህም ቢሆን በፍስፍናው የተማረኩ ልሂቃን ያደረጉት የከሸፈ ሙከራና አምባገነኖች ጠቃሚ ሁኖ ስላገኙት የሰሩበት ነው፡፡
ታሪካዊ ቁሳዊነት
የማርክሲዝም ምሁራዊ መሰረት ተደርጎ የሚወሰደው ይህ ታሪካዊ ቁሳዊነቱ ነው፡፡ የህብረተሰብ አደረጃጀት የሚወሰነው በኢኮኖሚያዊ መሰረቱ ነው፣ ላእላይ ቅርጽ ያልናቸው (ፖለቲካ፣ ርእዮተ ዓለም፣ ሕግ፣ ኪነ ጥበብ፣ ስነ ጽሑፍ፣ ስነ ምግባር፣ ሐይማኖት) በዚህ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ተጽእኖ ስር ናቸው ይላል፡፡
[13] ስለዚህም በሰው ልጆች ታሪክ የለውጥና እድገት መንስኤዎችን ከኢኮኖሚያዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ እና ባጠቃላይ ከቁሳዊ ምክንያቶች እና በጎሳዎች፣ መደቦች፣ ሃገሮች መሃከል በቁሳዊ ምክንያት የሚደረጉ ግጭቶችን ውስጥ ይፈልጋል፡፡
ብዙ ሃያስያን ይህ ሲበዛ የተቃለለ ምልከታ ነው ይላሉ፡፡ ማርክስ ላእላይ ቅርጽ ያላቸው ሃሳቦች፣ ባሕሎችና ሌሎችም ነጥቦች የህብረተሰቡን መስመር በመቀየስ የኢኮኖሚያዊ መሰረቱን ያክል ወሳኝነት አላቸው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ለምን ማርክስ ሃሳቦቹን አምርሮ ለማስፋፋት ይሰራል ብለው ይጠይቃሉ፡፡
ለዚህ ምላሽ የማርክስ አጋር የሆነው ፍሬደሪክ ኢንግልስ የሚከተለውን ይላል፡
“እንደ ቁሳዊ የታሪክ ምልከታ ከሆነ የመጨረሻው (ዋናው) የታሪክ ወሳኙ ነጥብ የእውነተኛ ሕይወት መመረትና መራባት ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ እኔም ማርክስም አልተናገርንም፡፡ እናም ማንም ይህን ጠምዝዞ ኢኮኖሚያዊ ነጥቡ ብቻ ነው ወሳኙ ቢል፣ ሃሳቡን ትርጉም ወደሌለው፣ ረቂቅ እና የማይገባ ሐረግ ቀየረው ማለት ነው፡፡”
[14]
ሆኖም እንዲህ ከተባለ ደግሞ ማርክሲዝም ሌላ እንከን ይመጣበታል፡፡ ላእላይ ቅርጹ መሰረቱ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ከሆነ ማርክስ ደጋግሞ የማህበረሰብ ታሪክ የኢኮኖሚያዊ መደቦች ግጭት ነው የሚለው ላያስፈልግ ነው፡፡ ይህ መላምቱም ተቀባይነት የለውም፡፡
ታሪካዊ ወሳኛዊነት
የማርክስ የታሪክ ንድፈ ሃሳብ የታሪክ ወሳኛዊነት (Historical determinism)
[15] እና ከዲያለክቲካል ቁሳዊነት የማህበራዊ ለውጥ መንገድ ነው ከሚለው ጋር ተሳስሮ የሚገኝ ነው፡፡
[16]ይህን በአንድ እድገት ደረጃ የምርት ኃይሎች ካለው የምርት ዘይቤ ግንኙነት ጋር ግጭት ይፈጥራሉ፣ ይህም የማህበራዊ አብዮት ዘመንን ያስጀምራል፡፡ የኢኮኖሚያዊ መሰረቱ ላይ የተከተለው ለውጥ ረዘመም አጠረም ከግዜ በኋላ ወደ አጠቃላይ የላእላይ ቅርጽ ለውጥ ያመራሉ፡፡
[17] ስለዚህም ሁሉ ነገር ቀድሞ በዚህ መልኩ የተወሰነ ነው ማለቱ ነው፡፡
ይህ ሃሳብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቀባይነቱን አጥቷል፡፡ ካርል ፖፐር ታሪካዊ ወሳኛዊነትን የታሪክ መጪው እርምጃን ማወቅ የማይቻል በመሆኑ ይህን ንድፍ ሃሳብ አጣጥሎታል፡፡ ጌሪ ሃበርማስም በበኩሉ ኸርነስት ናጄልን በማጣቀስ ታሪክ ቀድሞ የታወቀ ነው የሚለው የታሪካዊ ወሳኝነት ንድፈ ሃሳብን ስህተት ያሳየናል፡
“በመጀመርያ በታሪክ የእድገት (የለውጥ) ህጎች ወይም መስመሮች የሉም፡፡ የሆኑ ክስተቶች ከመሆናቸው በፊት በትክክል ልንገምትበት የምንችልበት መርሆዎች ወይም መሰረታዊ ጭብጦች የሉም፡፡ ሁለተኛ መጪውን ታሪክ መተንበይ አይቻለም፣ ምንም እንኳ ተደጋግሞ ተቃራኒው ቢባልም፡፡ ያለፉ ክስተቶች ወይም እንዲህ የመሰሉ መረጃዎች መጪውን ግዜ አይወስኑም፡፡ አራተኛ ያልተጠበቁ ወይም ከተለመደው ወጣ ያሉ ክስተቶች የታሪክ አካል ናቸው፡፡ አምስተኛው መከራከርያ የወሳኛዊነት ዓለም ጭብጥን ከሰው ልጆች ነጻነትና ሞራላዊ ኃላፊነት ጋር እንዲሄድ አድርገው ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ የሚፈጠረው ግጭት ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ነጻነት ከሰው ልጆች ምርጫ የሚመነጭ የታሪክ የፈጠራ ገጽታ ያስፈልገዋል፡፡ … ናጄል በድጋሚ ወሳኛዊነት በዘመናዊ ፊዚክስ የገጠመው ተቃውሞ የታሪክ ምሁራን ላይ ተጽእኖ በማሳደር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡”
[18]
የግለሰብ መብችን መጨፍለቅ
በኮሚዩኒስት ማኒፌስቶ ላይ 10 መደረግ ያለባቸው ነጥቦችን ብሎ ያስቀመጣቸው የግለሰብ መብቶች ጥሰት ናቸው፡፡ የመሬት ባለቤትነትን መብት ማጥፋት፤ በደሞዝ ልክ እየጨመረ የሚሄድ ግብር፤ የውርስ መብት ማጥፋት፤ ሃብት መውረስ፤ ገንዘብ ነክ የሆኑ ድርጅቶችን (ባንኮችን) በመንግስት ቁጥጥር ስር ማድረግ፤ መገናኛና ትራንስፖርት አገልግሎትን በመንግስት ቁጥጥር ስር ማድረግ ወዘተ. የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ነጻ ትምህርት እና ሕጻናትን ከፋብሪካ ሥራ መከልከል የሚለው ጥሩ ነገር ከተናገረ በኋላ ትምህርትን ከኢንዱስትሪ ጋር ማዋሃድ ይላል፣ ሌላ ትምህርት የፈለገስ ምን ሊሆን ነው?
ኢኮኖሚ የነጻነት አምድ እንደመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን መነጠቅ ሰብአዊ መብትህንም ማጣት ነው፡፡ ብዙ ኢኮኖሚስቶች የገበያ ልውውጥ መሪ ባልሆነበት አገር ጨቋኝ ፖለቲካዊ መሪዎች ማስገደጃ ኃይል ባለቤት እንዲሆኑ ያደርጋል ይላሉ፡፡ ተጠቃሹ ፍሬደሪክ ሃይክ ነው፡፡
[19]ሶሻሊስት የሚባለው ጆን ማይናርድ ኬንስም ሳይቀር ይስማማበታል፡፡
[20]ሁለቱም በአንዲት ሃገር ነጻነት እንዲያብብ ካፒታሊዝም ወሳኝ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በተጨማሪም ሃገራችንን ጨምሮ ማርክሲስታዊ አመለካከት እንዴትና የት እንደሚያደርስ በተግባር የምናውቀው ስለሆነ ተጨማሪ ማለት አያስፈልግም፡፡
የጋርዮሻዊነት ትግበራ
በተለይ አናርኪስቶች (መንግስት አያስፈልግም፣ በሰፈርና በሕብረት ስራ ተደራጅቶ ሕብረተሰቡ እራሱን በራሱ ያስተዳድር የሚሉ) ማርክሲስታዊ ኮሚውኒዝም መጨረሻ ላይ ወደ ማስገደድና የመንግስት የበላይነት ያመራል ብለው ይወቅሱት ነበር፡፡ ሚካኤል ባኩኒን የተባለው ታዋቂ አናርኪስት ማርክሲስታዊ መንግስታት ሕዝቡን አዲስና ቁጥራቸው ብዙም ባልሆኑ ባላባቶች አምባገነናዊ አገዛዝ ስር ወደ ማስገባት ነው የሚያመሩት ብሎ ነበር፡፡ በተጨማሪም እኚህ አዲስ ባላባቶች ከሰርቶ አደሩ ቢገኙም አዲስ የጨበጡት ኃይል ለሕብረተሰብ ያላቸውን ምልከታ በአብዩ እንደሚቀይርና ብዙሐኑን ሰርቶ አደሮች ዝቅ ዘድርገው እንዲያዩ እንደሚያደርጋቸው ባኩኒን ገልጾ ነበር፡፡
[21]ስለዚህም በተግባርም እንደታየው የሰርቶ አደሩ አምባገነንነት የሚወልዶው ጋርዮሻዊነት (ኮሚውኒዝም) ተግባራዊነት የማይኖረው የከሸፈ መላ ምት ነው፡፡
ስነ ምግባራዊ ሂስ
ግብ አካሄድን ያፀድቃል የሚለው፣ ማለትም ለመልካም ግብ እስከሆነ ደረረስ ክፉ ማድረግ ጥሩ ነው በሚል እምነት ማርክሲስታውያን ተወቅሰዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ከማርክስ የመነጨ አይደለም ብለው የሚከራከሩ አሉ፣ ማርክስ እንደሚከተለው ጽፏል በማለት፡
“ፍትሐዊ ያልሆነ አካሄድ የሚጠይቅ ግብ ፍትሐዊ ግብ አይደለም፡፡”
[22]
ሊዮን ትሮትስኪም በበኩሉ ዲያለክቲካል ቁሳዊነት የአካሄድና የግብ ጥንዳዊነት የለውም፡፡ ግቡ በተፈጥሮ ከታሪካዊ እንቅስቃሴ የሚመነጭ ነው፡፡ በተፈጥሮ አካሄዱ የግቡ ታዛዥ ነው ብሎ ነበር፡፡
[23]
ቃላት የተደረደሩት እንዲህ ቢመስሉም ፍትሃዊ ነው የሚሉት እስከምን ይደርሳል የሚለው እንዳለ ሁኖ ተከታዮቻቸው ካሳዩት አካሄድ ወቀሳ ነጻ አያወጣቸውም፡፡
ስነ እውቀታዊ (Epistemological) ሂስ
መደብ ወይስ ሕብረተሰባዊ ቅርጽ (ካስት)?
አንዳንዶች የማርክሳዊ የሕብረተሰብ አመለካከት መሰረታዊ ስህተት አለበት ይላሉ፡፡ ለምሳሌ መደብ እያለ የሚለየው በምእራቡ ህብረተሰብ የሌለ እና ከምስራቁ (ሕንድ) በዘር የሚወረስ የህብተረሰብ ቅርጽ (ካስት) ስርአት ጋር አንድ አድርጎ አቅርቦታል፡፡ በማርክስ ስሌት አንዱ መደብ ሌላው መደብ ላይ በማያሴሩ ምክንያት ወደ ግጭት ይሄዳሉ ሲል እውነቱ ግን በዛው መደብ ያሉ ሰዎች ከለሌላኛው መደብ ላይ ለመድረስ ከመደባቸው ውስጥ ካሉት ጋር ነው የሚፎካከሩት፡፡ ማርክስ በካፒታሊስት ማሕበረሰብ ያስቀመጣቸው የሚለዩ ናቸው፡፡ አባሎቻቸው ከፍና ዝቅ የሚሉ ናቸው፡፡ የመደብ አባልነት በዘር የሚወረስ አይደለም፡፡ የሚመደበው በግለሰብ ደረጃ የእለት ክንውኑ በሚያስገኝለት ተቀባይነት አንጻር ነው፡፡ ሕዝቡ ምርት በመግዛትና በመሸጥ ማን የፋብሪካዎች ኃላፊ መሆን እንዳለበት ይወስናል፣ ማን በቲያትር መተወን እንዳለበት ይወስናል፣ ማን በፋብካ መስራት እንዳለበት ይወስናል፡፡ ሃብታሞች ድሃ፣ ድሆች ሃብታም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ባርነት መወገዱ ላይ ሁሉም ባሮች ተጠቃሚነት አላቸው፣ ሆኖም ግን እንዲህ ያለ ግጭት ከሕግ በፊት ሁሉም እኩል በሆነበት ማሕበረሰብ አይኖርም፡፡
[24]
ሳይንስ ወይስ ዶግማ?
ፖፐር እንደሚሞግተው ከሆነ ታሪካዊ ቁሳዊነት ሱዶሳይንስ (ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ሳይከተል እንደ ሳይንስ የቀረበ የተሳሳተ እምነት) ነው ይለዋል፣ ምክንያቱም ደግሞ የሐሰት መሆኑን ማሳየት አይቻለምና፡፡ ፖፐር ማርክሲስታዊነት መጀመርያ ላይ ሳይንሳዊ ነበር፣ ማለትም ማርክስ ተንባይ የሆነ ንድፈ ሃሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ግምቶቹ (ትንቢቶቹ) እውን ሳይሆኑ ሲቀሩ ንድፈ ሃሳቡ ውድቅ መደረጉ (የሐሰት መሆኑን ከመታየት)ያወጣው ለእርሱ ሁኔታ ብቻ የሚሰሩ መላምቶች (አድ ሆክ ሃይፖተሲስ) በመጨመር ከእውነታው ጋር እንዲገጥም ሙከራ ተደርጓል፡፡ በዚህም መልኩ መጀመርያ ላይ ሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳብ የነበረው ወደ ሱዶ-ሳይንሳዊ ዶግማ ሊወርድ ችሏል፡፡
[25]
ማርክሲስታውያን ለዚህ ሂስ የሚሰጡት ምላሽ ሁሉም ማህበራዊ ሳይንሶች እንደ አካላዊ ሳይንስ ሙከራዎች ስላልሆኑና የተወሳሰቡ ክስተቶች ትንተና ላይ ስለሚመሰረቱ ሐሰትነታቸውን ማሳየት አይቻልም ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን ፓውፐር ይህን ተቀብሎ ይህንኑ መረጃ ማእከላዊ (መንግስታዊ) እቅድ አውጪነትንና ሁሉን አቀፍ ታሪክ ተንታኝ ርእዮተ ዓለሞችን ለማውገዝ ተጠቅሞበታል፡፡
[26]
ማርክስ ለምን ይወደዳል?
ቅሉ እንዲህ ከሆነ፣ ማርክስ በተግባርም በንድፈ ሃሳብም እንደተሳሳተ ማየት ከቻልን ለምን ዛሬ ድረስ ጽሑፎቹና መልእክቶቹ የሰው ልጆችን ልብ ይገዛሉ ብለን መጠየቃችን አይቀሬ ነው፡፡ ምላሹን እራሱን ጸረ-ካፒታሊስት እንደሆነ የሚቆጥር ግን ማርክሲስት ያልሆነ ሰው ከሰጠው ማብራርያ እናገኘዋለን፡፡
[27] ይህ ጸሓፊ ስለ ካፒታሊዝም ያለውን ምልከታ አልቀበልም፣ ሆኖም ግን ቀድሞ ማርክሲስት የነበረ በመሆኑ የማርክስ አማላይነትን ለመመስከር ብቁ ነው፡፡ ማርክስ በሶስት ዋና ምክንያቶች ይወደዳል፡ ትርጉም፣ ዓላማ እና ቅኔ ወይም ውበት፡፡
ማርክስ ለአንባቢዎቹ በታሪክ ትርጉም እና ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ የትልቅ፣ የዘመናት ጅረት አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ለማንኛውም የሚደርስባቸው ተስፋ መቁረጥና እምነት ማጣት ምትክ ይሆናቸዋል፡፡ “እኛ ማን ነን?”፣ “ለምድን ነው እዚህ የመጣነው?” ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሆናቸዋል፡፡
በማርክስ ታሪክ የመደብ ትግል ሰንሰለት ነው በዚህ ትግል አካል መሆን ደግሞ ዓላማ ይሰጣል፡፡ መደብ አልባ ምድራዊ ገነት የመፍጠር ዓላማ፡፡
ሌላው የማርክስ ጥንካሬ ታሪክ አተራረኩ ነው፡፡ ስለ ፖለቲካ፣ ፍልስፍናና ኢኮኖሚክስ የሚጽፍ እንደመሆኑ ደረቅ አጻጻፍ መከተል ነበረበት፡፡ ሆኖም ግን ማርክስ ሲጽፍ ውበት አለው፡፡ ለምሳሌ ኮሚኒስት ማኒፌስቶ ላይ፡ “ብዙሃኑ የሚያጡት ምንም ነገር የለም ከታሰሩበት ሰንሰለት በቀር፡፡ ድል የሚያደርጉት ዓለም አላቸው፡፡” ይላል፡፡ በዚሁ ስራ ብቻ እንኳ ሌላ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሆኖም ግን ሰዎች ከዚ አሻግረው በስሜት ብቻ ሳይሆን በመሰረተ-እውነትም መመራት ነበረባቸው፡፡ ማርክስ “ሃይማኖት የሕዝቡ አደንዛዥ እጽ ነው፡፡” የምትል አባባሉ ይታወቃል፣ ፖል ሳሙኤልሰን የተባለ ኢኮኖሚስት ደግሞ “ማርክሲስታዊነት የማርክሲስታውያን አደንዛዥ እጽ ነው፡፡” ብሎ ነበር ከዚህ ሁሉ ትንተና እና ያደረሰው ውድመት በኋላ አሁንም ሲያመልኩት በመታዘብ፡፡
አሁን ስንጀምር ያጣቀስነው የማርክስ አባባል ተገልብጦ እራሱ ላይ ሲሰራ ለማየት ችለናል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ያሉ ዋና ጥቅሶች ከተለያዩ መጣጥፎች የተወሰዱ ናቸው፡፡