በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲኦ ዞን ያለ መንጃ ፈቃድ እያሽከረከሩ ሰርግ ላይ የነበሩ ሁለት የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ የሞት እና በ12 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ያደረሱት የይርጋ ጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ በገደብ ቅጣት ( Probation) ተለቀቁ።
አደጋው የደረሰው በዞኑ ይርጋጨፌ ወረዳ ሀፉርሳ ወራቤ በተባለ ቀበሌ ታኅሳስ 13/ 2017 ዓ.ም ለልምምድ ብለው ያለመንጃ ፈቃድ የመንግሥት ተሽከርካሪ እያሽከረከሩ በነበሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ሚጁ መሆኑን የሟች ቤተሰብ እና የጌዲዮ ዞን ፍትሕ መምሪያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተሽከርካሪ አደጋው የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ገነት ንጉጆ የተባሉ ባለቤታቸው እና ወ/ሮ እዲኮ ዲቃዶላ የተባሉ እናታቸው የሞቱባቸው አቶ ኩራባቸው ሞሮማ “ላያቸው ላይ ነው የወጣው” በማለት ስለ አደጋው ተናግረዋል።
በወረዳው በአሽከርካሪነት የተቀጠሩ አንድ ሰራተኛ አስተዳዳሪው ለልምምድ ብለው ጋቢና ሹፌራቸውን አስቀምጠው ለማሽከርከር እንደወጡ የተናገሩ ሲሆን ተሽከርካሪው ሰርግ ላይ ድንኳን ውስጥ የነበሩ እድምተኞች ውስጥ “ዘሎ ነው የገባው” ብለዋል።
ተከሳሹ ስምንት ዓመት እንደተፈረደባቸው የሚናገሩት የሟች ቤተሰብ፤ ነገር ግን ስለመለቀቃቸው ከሰዎች እንደሰሙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የወረዳው ሰራተኛ የቀድሞው አስተዳዳሪው ስለመለቀቃቸው በአይናቸው ማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በጣም ነው የምናዝነው ” ሲሉ ለሰሙት ዜና ምላሽ የሰጡት ቤተሰብ “እስካሁን ወጥተንም አናውቅም፤ ሀዘን ላይ ነው ያለነው። የአንድ ሰው ሕይወት ብቻ አይደለም። ሁለት ሰው ከአንድ ቤት ማጣት ማለት ትልቅ ሀዘን ነው” ብለዋል።
ዐቃቤ ሕግ የወረዳውን አስተዳዳሪ “በቸልተኝነት የሰው ሕይወት ማጥፋት” እና “በቸልተኝነት የአካል ጉዳት ማድረስ” የሚሉ ሁለት ክሶች ማቅረቡን የዞኑ ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ዘውዴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።በዚህም ተከሳሹ ጥፋተኛነቱን በማመኑ ፍርድ ቤቱ የካቲት 28/ 2017 ዓ.ም. “የመነሻ ቅጣት” የሆነውን የስምንት ዓመት እስራት እና የ13 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ብይን መስጠቱንም ገልፀዋል።
ተከሳሹ ያቀረቧቸውን ሰባት የቅጣት ማቅለያ ሀሳቦችን ፍርድ ቤቱ በመቀበል ቅጣቱን ወደ ሦስት ዓመት ከሰባት ወር እስራት ስለማውረዱን አክለው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ይህንን ቅጣት ፍርድ ቤቱ “በማገድ” ተከሳሹን የሁለት ዓመት የገደብ ቅጣት (probation) በመስጠት እንዳሰናበተው አስታውቀዋል።
መጋቢት 5/ 2017 ዓ.ም. ለመጨረሻ ውሳኔ የግራ የቀኝ የቅጣት አስተያየት የቀረበለት ፍርድ ቤቱ “የወንጀል ሕጉን 192” መሰረት በማድረግ የሁለት ዓመት የገደብ ቅጣት ብይን መስጠቱን ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“[በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ] ለፍርድ ቤት [ከወንጀሉ] ክብደት እና ቅለት እንዲሁም የስነ ስርዓት ሕጉ ከሚፈቅደው አግባብ ሊገድብ ይችላል የሚል የተሰጠ ስልጣን አለ።
በመጨረሻም ያንን ቅጣቱን ማረሚያ ቤት መግባት ሳያስፈልግ በሁለት ዓመት የገደብ ቅጣት ውስጥ፤ ውጭ ሆኖ ይጨርስ የሚል ብይን ሰጥቶታል” ሲሉ ስለ ፍርዱ አብራርተዋል።

“ሁለት ዓመት የገደብ ቅጣት” (probation) ምን ማለት እንደሆነም ሲያብራሩ “ለሁለት ዓመት ከየትኛውም አይነት ወንጀል ራሳቸውን አቅበው፤ የትኛውም የወንጀል ድርጊት ላይ እንዳይገኙ [ነው]። ሆነው [ተሳትፈው] ቢገኙ ግን የታገደው የቅጣት ውሳኔ ተፈፃሚ ይሆናል” ብለዋል።
ዐቃቤ ሕግ የፍርድ ቤቱ ውሳኔው “ፍትሐዊ አይደለም” በሚል ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረቡን አቶ ብዙአየሁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ይህን ያህል የቅጣት ማቅለያዎችን ተቀብሎ፤ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የቅጣት ማክበጃ ሀሳቦችን ዘሎ ፍርድ ቤቱ ባልተገባ መልኩ ቅጣቱ ወደ ታች እንዲወርድ ያደረገበት አግባብ አሰራርን፤ ሕግን መሰረት ያደረገ አይደለም። ከዚህ ባለፈም [ፍርዱ] ሊገደብ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። የሚታገዱ ጉዳዮች ሌሎችን ሊያስተምሩ የሚችሉ፤ . . . ግለሰቡ ለማኅበረሰቡ ጥቅም የሚያመጣ ከሆነ ነው” ብለዋል።
በቸልተኝነት የሰው ሕይወት ማጥፋት ከሰባት ዓመት እስከ 15 ዓመት እስራት የሚስቀጣ ወንጀል ሲሆን፤ በቸልተኝነት አካል ጉዳት ማድረስ ደግሞ ከሦስት ዓመት በላይ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።
የተከሳሹ ቅጣት አነስተኛ ለመሆኑ መንግሥት ባለስልጣን መሆናቸው ሚና ተጫውቶ እንደሆነ የተጠየቁት የፍትሕ መምሪያ ኃላፊው፤ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዳይመሰርት ተፅዕኖ እንዳልደረሰበት በመጠቆም ‘ሚና ነበረው’ የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ዜና ምንጭ BBC News https://www.bbc.com/amharic/articles/c4g0yqwx9leo