Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

$
0
0
የምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሃንስ ተሰማ
የምስሉ መግለጫ,የምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሃንስ ተሰማ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ስር ዋሉት ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ቅዳሜ ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ያለመከሰስ መብታቸውን የተነሳው የምክር ቤት አባል አቶ ዮሃንስ ተሰማ፤ ከአንድ ሳምንት እስር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

አቶ ዮሃንስ የቀረቡበት የአሶሳ ዞን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ በምክር ቤት አባሉ ላይ 14 የምርመራ ቀናትን መፍቀዱን ባለቤታቸው እና አንድ የፓርቲው ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዛሬ ሰኞ መጋቢት 8/2017 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡት የተቃዋሚው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) አመራር አቶ ዮሃንስ፤ በምክር ቤት አባልነታቸው ያገኙት ያለ መከሰስ መብት ሳይነሳ በቁጥጥር ስር ዋሉት የካቲት 30 ነበር።

አቶ ዮሃንስ በቁጥጥር ስር ዋሉት፤ ቦዴፓን ከወከሉ ሁለት የምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን የተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግሥት እና የተወካዮች ብዛት ያሻሻሉት አዋጆች “ተፈጻሚ እንዳይሆኑ” ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ አቤቱታ ካቀረቡ ከአምስት ቀናት በኋላ ነበር።

የምክር ቤት አባሉ ከታሰሩ በኋላ፤ “ቃላቸውን እንዲሰጡ በመርማሪ ፖሊሶች” ቢጠየቁም፤ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ይህንን እንደማያደርጉ ሲገልጹ መቆየታቸውን ምንጮች ተናግረው ነበር።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትህ ቢሮ፤ ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሰረትም ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ መጋቢት 6/2017 ዓ.ም. የአቶ ዮሃንስ ያለመከሰስ መብት ተነስቷል።

የምክር ቤት ያለመከሰስ ከለላቸው እንዲነሳ የተጠየቀው፤ አቶ ዮሃንስ አቤቱታ ያቀረቡባቸው የአዋጅ ማሻሻያዎች ከጸደቁበት የምክር ቤት ጉባኤ በኋላ በተፈጸሙ ድርጊቶች በመጠርጠራቸው እንደሆነ የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ሀሚድ በአስቸኳይ ጉባኤው ላይ ተገኝተው ከጠቀሷቸው ድርጊቶች መካከል፤ “ግጭትን የሚቀሰቅሱ፣ የክልሉን እና የምክር ቤቱን ክብር የሚነኩ እና ሞገሱን ዝቅ የሚያደርጉ መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ማሠራጨታቸው” የሚለው ይገኝበታል።

ይህ ድርጊታቸውም “ሕዝብን ለብጥብጥ የሚያነሳሳ” እንደሆነ የቢሮ ኃላፊው እንደተናገሩ ምክር ቤቱ በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ ጠቅሷል።

አቶ ዮሃንስ፤ “ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት እና ለመነጠል የማነሳሳት በመስራት” እና “ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት” እንደተጠረጠሩም ተገልጿል። “መንግሥትን በኃይል ለመናድ ከሚጥሩ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አመላካች መረጃዎች” እንዳሉም ተነግሯል።አቶ ዮሃንስ፤ በእነዚህ ጉዳዮች እንደተጠረጠሩ ማብራሪያ የቀረበለት የክልሉ ምክር ቤትም፤ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ወስኗል።

የምክር ቤት አባሉ ዛሬ ረፋድ ላይ ፍርድ ቤት ሲቀርቡም መርማሪ ፖሊስ በእነዚሁ ድርጊቶች እንደጠረጠራቸው ማስረዳቱን በችሎት ውሎው ላይ የተገኙ የፓርቲው ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የክልሉን ሕገ መንግሥት ለመናድ መንቀሳቀስ”፣ “ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር”፣ እንዲሁም “የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች መሳደብ” አቶ ዮሃንስ የተጠረጠሩባቸው ድርጊቶች እንደሆኑ መገለጹን ምንጩ አስረድተዋል።

“የክልል ምክር ቤት የወሰነው ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ታች ላለው ኅብረሰተብ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት” እና “በማህበራዊ ሚዲያ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክት ማስተላለፍ” ድርጊቶችም ተጠርጥረዋል ተብሏል።

መርማሪ ፖሊስ፤ በአቶ ዮሃንስ “ስልክ ላይ የፎረንሲክ ምርመራ ለማካሄድ” እና “የተለያዩ ማስረጃዎችን ማደራጀት” የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ለችሎቱ ጥያቄ ማቅረቡን የፓርቲው ምንጭ አስረድዋል።

ከመርማሪ ፖሊስ በኋላ የመናገር እድል ያገኙት አቶ ዮሃንስ በበኩላቸው “አንድ ሰው ሕገ መንግሥት ለመናድ ተንቀሳቀሰ የሚባለው ኃይል ሲኖረው፣ የተደራጀ የጦር ካምፕ ሲኖረው እና ይህም በመረጃ ሲረጋገጥ” እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

“የእኛ ድርጅት፣ እንደ ግለሰብም ይህንን አናሟላም። የዚህም ተሳታፊ አይደለንም” እንዲሁም “ሕገ መንግሥት ለመናድ ያደረግኩት ነገር የለም” ሲሉ ራሳቸውን መከላከላቸውን ምንጩ ገልጸዋል።

“ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር” በሚል የተገለጸውን በተመለከተም፤ “የውጭ ኃይል” የተባለው አካል የትኛው እንደሆነ በግልጽ አለመጠቀሱን በማንሳት መልስ ሰጥተዋል ተብሏል።

የምክር ቤት አባሉ በራሳቸው የፌስቡክ ገጽ ካሰፈሯቸው ጽሑፎች መካከል “የሚያስጠይቅ ካለ እንዲቀርብ” ጠይቀው፤ “ሀሰተኛ አካውንቶች የሚባሉት እኔንም፣ ድርጅቴንም አይወክሉም” ሲሉ መናገራቸውን ምንጩ ጠቅሰዋል።

እንደ ምንጩ ገለጻ፤ መርማሪ ፖሊስ ያነሳቸው ጉዳዮች “የዋስትና መብት እንደማያስከለክሉ” እና “የምርመራ ጊዜ የሚያስፈልግ ከሆነም ይሰራል የተባለው ማጣራት 14 ቀናትን የማይወስዱ” መሆናቸውን አቶ ዮሃንስ ተናግረዋል።

ለዚህ ምላሽ የሰጠው መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አቶ ዮሃንስ የተጠረጠሩበት “ከውጪ ኃይል ጋር ግንኙነት የመፍጠር” ድርጊትን ለመመርመር “ከ14 ቀናት ውጪ በቂ አይደለም” ማለቱንም አስረድተዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የአሶሳ ዞን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም፤ መርማሪ ፖሊስ የተጠቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለመጪው መጋቢት 22/2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>