በአማጺያን እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄደባት ባለችው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ ቢያንስ 53 ሰዎችን መግደሉ ተገለጸ።
በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ውስጥ በተከሰተው በዚህ ገዳይ በሽታ የተያዘ ሰው የበሽታው ምልክት ከታየበት በኋላ በአንድ ቀን ውስጥ ለህልፈት እንደሚዳረግ ተነገሯል።
በበሽታው ሰበብ ሰዎች እየሞቱ መሆናቸው የታወቀው እየተጠናቀቀ ባለው የካቲት ወር ውስጥ ሲሆን፣ ስፍራውም ኢኩዌተር በተባለው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ግዛት በምትገኘው ባሳንኩሳ መንደር ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው ይህ ምንነቱ ያልታወቀ ገዳይ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሠራጨቱ ስጋት ዝቅተኛ ነው።
ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ገድሏል የተባለው በሸታ መነሻ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እና የመተላለፊያ መንገዶቹ እስካሁን በግልጽ አልታወቀም።
በበሽታው ከተያዙ ሰዎች በተወሰዱ ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ፤ ግለሰቦቹን ለሞት የዳረጋቸው ኢቦላ ወይም ማርበርግ የተባሉት በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎች አለመሆናቸው ተረጋግጧል።ከናሙናዎቹ መካከልም ግማሾቹ የወባ በሽታ ምልክት እንደተገኘባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ባለሙያዎች ወባን የመሳሰሉ በሽታዎች በሚከሰቱባቸው ቦታዎች በማጋጠም የተለመደ የሆነው በባክቴሪያ የሚተላለፈው የማጅራት ገትር በሽታ ሊሆን ከቻለ በሚል ምርመራ እያካሄዱ ነው።
በተጨማሪም በሽታው በተከሰተበት ቦታ የኬሚካል መመረዝ አጋጥሞ እንደሆነ ለማጣራት ለምርመራ የውሃ እና ሌሎች አካባቢያዊ ናሙናዎችን ሰብስበዋል።
እስካሁን ከተመዘገቡት ሞቶች መካከል የመጨረሻው የተከሰተው ከአንድ ሳምንት በፊት መሆኑ ተነግሯል።
በዚህ ምንነቱ ባልታወቀ ክስተት ምክንያት ለህልፈት የተዳረጉት ሰዎች በተለያየ የዕድሜ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ጎልማሳ እና ወጣት ወንዶች በብዛት ይገኙበታል።
ህመሙ ያጋጠማቸው ሰዎች ላይ የሚታዩት ምልክቶች በርካታ እና የተለያዩ ናቸው። ከምልክቶቹ መካከል ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ ተቅማጥ፣ ማላብ፣ ማዞር፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
የጤና ችግሩ ባጋጠመበት አካባቢ ከአንድ ሺህ ሦስት መቶ በላይ ሰዎች ላይ ትኩሳት እንዲሁም ከተጠቀሱት የህመም ምልክቶች መካከል ቢያንስ አንዱ ታይቶባቸዋል።
በምድር ወገብ አካባቢ የምትገኘው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባላት ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ከሚገኙ የዱር እንስሳት በሚነሱ የበሽታ አምጪ ተዋህሲያን ምክንያት፤ በተደጋጋሚ የተለያዩ በሽታዎች ወደ ሰዎች ሲተላለፉ ቆይተዋል።
በቅርቡም ኢቦላ እና ኤም ፖክስ በአገሪቱ እና በአጎራባች አገራት ውስጥ ተከስተው ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆናቸው አይዘነጋም።