Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

በማንቸስተር ዩናይትድ ታሪክ ደካማው ቡድን ሳይሆን አይቀርም- ሩበን አሞሪም

$
0
0
የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ቡድናቸው በክለቡ 147 ዓመታት ታሪክ “በጣም ደካማው” ሳይሆን እንደማይቀር ገለጸ።

ቡድኑ በብራይተን 3 ለ 1 የተሸነፈበት ጨዋታ በሜዳው ካደረጋቸው ያለፉት አምስት የፕሪሚር ሊግ መርሐ ግብሮች በአራቱ የተሸነፈበት ሆኗል።

አሞሪም ኤሪክ ቴን ሃግን ተከቶ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ፖርቹጋላዊው ካለፉት 11 ጨዋታዎች 11 ነጥብ ብቻ ሰብስቧል።

ዩናይትድ ከመውረድ ቀጠና በ10 ነጥብ ርቆ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

“ካለፉት 10 የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ነው ያሸነፍነው። ይህ ለደጋፊዎቹም ሆነ ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት” ብሏል።

“አዲሱ አሰልጣኝ ካለፈው አሰልጣኝ በበለጠ እየተሸነፈ ነው። ይህንን አውቃለሁ።”

“በማንቸስተር ዩናይትድ ታሪክ ደካማው ቡድን ሳንሆን አንቀርም። እናንተ [መገናኛ ብዙሃን] ርዕስ እንደምትፈልጉ ባውቅም እውነቱን ተናግሬ መቀየር ይኖርብኛል። ይኸው ርዕስ ሰጠዋችሁ” ሲል ተናግሯል።

በብራይተን ጎል ካስተናገደ በኋላ ዩናይትድ አቻ ለመሆን በቅቶ ነበር።

የብሩኖ ፈርናንዴስ ፍጹም ቅጣት ምት ቡድኑን ያነቃቃዋል ቢባልም ይበልጥ ተበልጦ ታይቷል።

ካኦሩ ሚቶማ ቡድኑን ቀዳሚ ሲያደርግ ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና የፈጸመውን ስህተት ተጠቅሞ ጂዮርጂኖ ረተር ለቡድኑ ሦስተኛዋን ጎል ከመረብ አሳርፏል። ለመሆኑ ይህ ቡድን በጣም ደካማው ይሆን?

ቁጥሮችን መመልከት ከቻልን ሩበን አሞሪም ቡድኑ በዩናይትድ ታሪክ “ደካማው ሳይሆን አይቀርም” ማለቱ የተጋነነ ሳይሆን አይቀርም። በሁሉም ረገድ ግን አጋኗል ማለት አይቻልም።

በ22 ሳምንት የሊጉ ጉዞ ከአሁኑ ቡድን ያነሰ ውጤት የነበራቸው 13 የዩናይትድ ቡድኖች ነበሩ። ይህ ግን ለመጨረሻ ጊዜ የሆነው እአአ በ1986-87 የውድድር ዓመት ነበር።

የአሁኑ ቡድን ደካማ ጉዞ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡

  • ከአውሮፓውያኑ1893/94 በኋላ በሜዳቸው ካደረጓቸው 12 ጨዋታዎች በስድስቱ የተሸነፈው የአሁኑ ቡድን ነው።
  • ባለፉት አምስት የኦልድ ትራፎርድ ጨዋታዎች ቀድሞ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። በአውሮፓውያኑ 2023 ተመሳሳይ ጉዞ ካደረጉ በኋላ የተመዘገበም ሆኗል።
  • ቡድኑ ካለፉት 22 ጨዋታዎች በ10ሩ ተሸንፏል። በአውሮፓውያኑ 1989/90 ወዲህ በፍጥነት ሁለት አሃዝ ሽንፈት ያስዘመገቡበት የውድር ዓመት ሆኗል።

ዩናይትድ ለአምስት ጊዜ ከሊጉ ወርዷል። ለመጨረሻ ጊዜ ቡድኑ የወረደው በአውሮፓውያኑ 1974 ነው። ይህ ቡድን ከሊጉ የሚወርድ ባይመስልም “ሊሆን ይችላል” ሲሉ አሰልጣኙ ባለፈው ወር ተናግሯል።

“ከሩበን አሞሪም የተሰጠ ጠንካራ መግለጫ ነው። ቋሚ አሰላለፋቸው 391 ሚሊዮን ፓውንድ ተከፍሎበታል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ደግሞ ለአምስት ተጫዋቾች 182 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍለዋል” ሲል የቀድሞው የኤቨርተን አማካይ ሊዮን ኦስማን ለቢቢሲ ማች ኦፍ ዘ ዴይ ተናግሯል።

“እንደዚህ መባል እኔን አያስደስተኝም። የትኛውም ተጫዋች በክለቡ ታሪክ የመጥፎው ቡድን አባል መባልን አይፈልግም። ምናልባትም እውነቱን ይሆናል።”

ብሩኖ ፈርናንዴዝ

‘ምንም ቢፈጠር እኔ አልቀየርም’

አሞሪም ከጨዋታው በፊት ከቀድሞው የክለቡ ታሪካዊ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉስን ጋር ረዥም ውይይት አድርጓል።

“በጎ እንዳስብ” ነግረውኛል ሲል አሞሪም ከቀድሞው አሰልጣኝ ጋር ስለነበረው ቆይታ ለቢቢሲ ራዲዮ 5 ተናግሯል።

ባለፉት ጨዋታዎች ክለቡ በሜዳው ማሸነፍ የቻለው በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን ሳውዝሃምፕተንን ነው። በጨዋታውም ለረዥም ደቂቃ ሲመራ ቆይቶ ባለቀ ሰአት አማድ ዲያሎ ባስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች ለማሸነፍ ችሏል።

አሞሪም ያለበትን ከባድ ኃላፊነት እንደሚረዳ አስታውቋል።

ቀድሞው የስፖርቲንግ ሊዝበን አሰልጣኝ 3-4-3 አሰላልፍን እንደማይቀይር ገልጿል። አሰላለፉ በፖርቹጋል ውጤታማ ቢያደርገው የዩናይትድ ተጫዋቾች ለመላመድ እንደከበዳቸው አስታውቋል።

“አዲስ አስተሳሰብ ማስረጽ ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ። በጣም ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ማወቅ ያስፈልጋል። ማሸነፍ ሲያቅትህ እና በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን ስትሸነፍ ደግሞ ነገሮች ይበልጥ ይከብዳሉ” ብሏል።

“ሁሉም ደካማ ብቃት እያሳየ ነው። ይህንን ማመን አለብን። ብዙ ጨዋታዎችን መሸነፍ ተቀባይነት የለውም። ተጋጣሚዎቻችን በብዙ ረገድ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ።”

“ወጥ አቋም እያሳየን ካለመሆኑም በላይ እኔም ተጫዋቾቼን መደገፍ አልቻልኩም። በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ደካማ ክብረ ወሰኖችን እየሰበርን ከመሆኑም ባለፈ በሜዳችን እየተሸነፍን መሆናችንን ማመን አለብን።”

“እንደሚሳካልን ባውቅም ግን የዋህ አይደለሁም። ይህንን ጊዜ ማለፍ አለብን። ምንም ቢፈጠር ግን እኔ አልቀየርም” ብለዋል።

ትልቅ መልሶ ግንባታ ያስፈልጋል

ማንቸስተር ዩናይትድን ተፎካካሪ ለማድርግ ትልቅ መልሶ ግንባታ ያስፈልጋል። በርካታ ተጫዋቾችም መልቀቅ ሳይኖርባቸው አይቀርም።

81.3 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቶበት በክለቡ ታሪክ ሁለተኛው ውዱ ተጫዋች ለመሆን የበቃውን አንቶኒን ለመውሰድ ሪያል ቤቲስ ሙከራ እያደረገ ነው።

ታይሬል ማላሲኣን ለማስፈረምም የፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በርካታ ክለቦች ፍላጎት አሳይተዋል።

ክርስቲያን ኤሪክሰን እና ቪክተር ሊንደሎፍ በሰኔ ወር ውላቸው ሲጠናቀቅ ቡድኑን እንደሚለቁ ይጠበቃል።

በ375 ሺህ ፓውንድ የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ የሆነውን ካሰሚሮን ለመውሰድ የሚፈልግ ካለም ሊለቀቅ ይችላል።

አጥቂው ማርከስ ራሽፎርድም ክለቡን ለመልቀቅ በሂደት ላይ ነው። “የእኔ ምርጫ ነው። ራሽፎርድ በአሁኑ ጊዜ ከቡድኑ ውጭ ነው። ለቡድኑ ጥሩ ነው ብዬ የማላስበውን ተጫዋች ማካተት አልፈልግም” ሲል አሞሪም አስታውቋል።

አሊሃንድሮ ጋርናቾን ለማስረም ናፖሊ ያቀረበውን ጥያቄ ዩናይትድ ውድቅ ቢያደርገውም የ20 ዓመቱን ተጫዋች ለማስፈረም ቼልሲን ጨምሮ በርካታ ክለቦች ፍላጎት አላቸው።

አሞሪም ለአሰላለፉ የሚፈልገውን ተጫዋች ለማስፈረም ከቡድኑ መሸጥ የሚኖርባቸው ተጫዋቾች ይኖራሉ።

አንድሬ ኦናና ደግሞ በሚዋዥቅ አቋሙ በመግፋት በቀላሉ የሚይዘውን ኳስ መቆጣጠር ባለመቻሉ ብራይትን ሦስተኛ ጎል እንዲያስቆጥር ዕድል አመቻችቷል።

“[እሱም] እንደቡድኑ ላይ ታች እያለ ነው። ከፍ ሲል በጣም ከፍ ይላል፤ ሲወርድ ደግሞ በጣም ይወርዳል” ሲል ስለ ግብ ጠባቂው አሞሪም ተናግሯል።

አንድ መልካም ነገር ቢኖር ቡድኑ የ17 ዓመቱን ፓራጓዊውን ተካላካይ ዲጎ ሊዮንን ማስፈረሙ ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>