ከሥርጉተ ሥላሴ 08.03.2015 /ሲዊዘርላንድ ዙሪክ/
የ2015 ዓለምዓቀፍ ሴቶችን ቀን እኔ በግሌ ዕለቱን ያሰብኩትን መጠነ ሰፊ አቅም ዬነበረውን በወንበዴው በወያኔ ትእቢት በቀላጤ የፈረሰውን የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲን፤ እስረኛዋን እናት ሀገሬን፤ እስረኛ እህትና ወንድሞቼን፤ በራህብ – በመፈናቀል ሰቆቃ ላይ ያሉ ወገኖቼን አስቤ ነበር። አንድነት ፓርቲ ዬብሄራዊነት ምንጩ ከቅንጅት መንፈስ የተነሳ ብቻ ሳይሆን የሴቶችን አቅም ያዳመጠ በኽረ ፓርቲ በመሆኑም ጭምር ነው….
አንድነት ለእኛ ትውልድ፤ እኛ ለተፈጠርንበት ትውልድ፤ የመጀመሪያዋን ሴት የፓርቲ መሪ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳን በብሄራዊ ደረጃ እንድትመራ፤ እንድታስተባብር የፈቀደ ብቸኛው ፓርቲ ነው። አንጋፋነቱን ሆነ የትውልድ ልዑቅ ፓርቲ መሆኑን ማመሳከር የሚችለው ሃቅም ይኼው ነው። የሴቶችን አቅም ፍሰት በዚህ ዙሪያ ቆጥቦልናል። ለአንድነት ፓርቲ ስለ ሴቶች የማድረግ ሙሉ አቅምና ሥጦታ ቅስቀሳ አያስፈልገውም ነበር። ዛሬ አንድነት የለም። አፍርሰዉታል። ንደውታል፤ ዘርፈውታል፤ መንፈሱን ቀምተውታል፤ ብቃቱን አራቁተውታል። እንዲህ እንደ ሚታየው ፎቶ ዕንባችን ከውስጥ ሞልቶ ውጩንም አርሶታል። የምር መራራ ቀን ነበር ….
እኔ የአንድነት መፍረስ የሰማሁ ዕለት ሰውነቴ ተቆረሰ፤ መንፈሴ ተናዳ፤ ህሊናዬ ቆሰለ። አንድ ብሄራዊ ፓርቲ ፈቃድ ተሰጥቶት ከተደራጀ በኋላ፤ ጊዜውን፣ አቅሙን፤ ጉልበቱን አፍስሶ ከሁሉ በላይ መሪዎቹን በተለያዬ ጊዜ ለካቴና – ለስለት፤ ለድብደባ – ለመደፈር ሰውቶ እንዲህ መስዋዕትነቱን ሁሉ መና በማደረግ ሲፈርስ ማዬት ከዚህ የበለጠ የሃዘን ቀን አልነበረም ለእኔ። ሁላችሁም እንደምታውቁት 90 ሚሊዮን ህዝብ ልሰደድ ቢል አይችልም፤ ጫካ ልግባ ቢልም እንዲሁ፤ ስለሆነም ነበር አንድነት አቅሙ የፈቀደውን የህዝብ አንጡራ ፍላጎት መርሁ በማድረግ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ከባርነት ለመላቀቅ፤ ቀጥሎም ዴሞክራሲን ለማስፈን ትግል ማደረግ ግድ ይለው ስለነበር አብዝቶ መስዋዕትነቱን የተቀበለ።
ሰላማዊ በሆነ መንገድ የታገሉ መሪዎቹ ሲታሰሩበት አዲስ በመምረጥ፤ ሲደበደቡበት በመንፈስ ከጎናቸው በመሆን፤ ሲሳደዱበት በማበረታታ፤ በሆደ ሰፊነት የአመራር ተካታታይነቱ በወያኔ ጣልቃ ገብነት ባልተቋረጠ ሁኔታ ቢደፈርስበትም ሳይታክት እርግብን አምኖ፣ ዘንባባን ተደግፎ ብዙ በጣም ብዙ ጥረት አድርጓል። ይቻላል – ይቻላል ይቻላል እያለ …. ጣረ ታገለ ታተረ …. ግን …. ሞት ተበዬነበት።
ከሁሉ በላይ ለእኔ መንፈስ እጅግ ቅርብ የሆነው የአንድነት ጉዳይ የኢትዮጵያ ሴቶችን ልዩ ብልህ አቅም ዕውቅና የሰጠ ብቸኛው ብሄራዊ ፓርቲ መሆኑ ነበር። 40 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ፓርቲዎች ሁሉ ያለደረጉትን ነገር ነበር አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ደፍሮ ያደረገው። በሌላ በኩልም አስተውላችሁት ከሆነ የአውሮፓ ኮሚሽን ዕንባችን የተጋራው ወላዊ የነፃነት ትግል ብርቱ ዕውቅና ዓርማው ሴት ነበረች። ክብርት ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ። ጋዜጠኛ ርዕዮትም የአንድነት ፓርቲ የምክር ቤት አባል ነበረች። ምንም እንኳን ከተገለሉት ውስጥ የነበረች ብትሆንም መነሻ ቤቷ አንድነት ነው። የእውነት መጨረሻው እውነት ነውና እውነተኞች ነጥረው አሁንም ጥቃት ስፈጸምባቸው ክብርት ጋዜጠኛ ርዕዮትና ሌሎች ቀደምት የአንድነት መሪዎች የተገለሉበት ሃቅ ዘመን ሰጠው።
40 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ፓርቲዎች ወይንም 23 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የጎሳ ድርጅቶች አንድ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ያላት ሴት ወይንም መሪ ወይንም ጋዜጠኛ አላፈሩም። አንድነት ግን አለው። በእኛ የሴቶች ታሪክ ውስጥ ልዩ ማህደረ – ዝክረ ነው። የአንድነት ሚስጢር ያለው ከዚህ ላይ ነው። አንድነት የመጀመሪያ የህይወት ትምህርት ቤት የሆነችውን እናት – ሴት – እህት – ሚስት – ጓደኛን፤ ጸጋ አልተላለፈም። ይህን ሃቅ የደፈረ- ያስተማረ – በተግባር አንድነት ብቻ ነው። ሴት እኔን ትምራኝ ብሎ መፍቀድ ከውሳኔዎቹ ሁሉ እጅግ ፈታኙ ነው። ይህን ጀርመኖችም ሲዊዞችም አድርገውታል። ውጤቱንም አዬተውታል።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሴቶች አትኩሮት፤ አክብሮት፤ ልቅና የሰጣቸውን ፓርቲያቸውን በማንለኝበት ወያኔ በቁሙ ሲያፈርስባቸው መቆጣት አለባቸው፤ መበሳጨት አለባቸው፤ ስለምን? ብለው መንገብገብ አለባቸው፤ ጉዳያችን ነው ብለው በባለቤትነት ስሜት ፊት ለፊት ወጥተው በሰላማዊ መንገድ ተራጋጩን የወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንፌስቶ አስፈጻሚዎች መጠዬቅ አለባቻው። ትእቢተኛውን የጎሳ ድርጅት መልስ እንዲሰጣቸው በተከታታይነት መጠዬቅ አለባቸው።
ቢያንስ የትዕቢተኛውን ትብትብ መንፈስ ክፍተት ከውስጡ መፍጠር አለባቸው። ንፋስ አብጠልጥሎ አናቱን እንዲፈርሰው ተግተው መጠዬቅ አለባቸው። በፌስ ቡክ፣ በቲተር፣ ወይ በጉጉል ወይ በግልጽ ደብዳቤ ሊሆን ይችላል። እርግጥ የብሄራዊ ነፃነት መፍጫው የምርጫው ክፍለ ጊዜ ሲያልፍ የሚኖር አዲስ የድብብቆሽ ትወና ሊኖር ይችላል። የሆነ ሆኖ ለዘለቄታ – ከባርነት ወደ ነፃነት፤ ከጭቆና ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገር ብቻ ሳይሆን የሴቶችን የመሆን አቅም በእኩልነት እስኪሰፍን ድረስ መትጋት ግድ ይላል። የአንድ ሀገር ዴሞክራሲ መጠን የሚለካው ለሴቶች ከሚሰጠው ዕውቅና ስፋትና ጥበት ይወሰናልና።
እኛ እንዳለፍነበት ዘመን የኢትዮጵያሴቶች አቅም መባከን ወይንም ከከርሰ ምድር ውስጥ እንዳለ ሃብት አፈር ለብሶ መቅረት የለበትም። አዲሱ ትውልድ ሴቶች ከወንዶች ጋር ተወዳድረው በሴትነታቸው ሳይሆን በመጠነ ሰፊ ብቃታቸው፤ በእናታዊ ጸጋቸው፤ በድርጁው መንፈሳቸው፤ በሚስትነት ስጦታቸው፤ በመምህርነት ክህሎታቸው፤ በማህበራዊነት መክሊታቸው ማሸነፍ አለባቸው። ዘመኑንም – መምራት። የእኔ ህልምና ናፍቆት ዬአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የአውሮፓ ኮሚሽን አሜሪካን ጨምሮ የበርካታ ሀገሮች መሪዎች ሴቶች እንዲሆኑ ነው። ከሴቶች ውስጥ ያለውን ሚስጢር ማንም ፈላስፋ ወይንም ሳይንቲስት ተመራምሮ እስካሁን አልደረሰበትም። ለነገሩ በሴቶች የብቃት ልክ ምን የምርምር ሥራ ተሰርቶ በፍጹም ሁኔታ የተዘለለ አምክንዮ ክስተትም ነው። ሴቶች ፍቅር ናቸው። ፍቅር ደግሞ ሁሉንም ነው መሬት ….
ኢትዮጵያ ሀገራችን በነገው የሴቶች ዓለም ትደምቅ ዘንድ፤ ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ፤ ሴቶች ዛሬን አብረው መሆን አለባቸው ነገን ለማግኘት። ግፊያው አለ፤ ግን ስልቱም ስላለ ማሸነፍ ይችላሉ – አይበገሬነት ከጠጡ፤
ሰሞናቱን ጀርመኖች በሁሉም ፓርቲዎቻቸው ጉልህ አጀንዳው በሴቶች እኩል ተሳትፎና ውጤት ግምገማ ላይ ነበሩ። ለዛውም በተመጠነ የቁጥር ተዋፆ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ተሰትፎ ባለበት ሀገር … እኔ ንጉሥ ዳዊት „የቤትህ ቅናት በላኝ” እንዳለው ነበር ያደረገኝ
ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ሲባል ደግሞ የትውልድ ፈርጦች የነገ ፍሬዎች „ነፃነት” ባሉ የጣይቱ ልጆች ባለፈው ዓመት ምን እንደደረሳባቸው ይታወቃል። ዱላ፤ እስር መደፈረ የዓለም ሴቶች የ2014 ቀናቸውን በፍሰሃና በደስታ ሲያሳልፉ የኢትዮጵያ ሴቶች ደግሞ በወያኔ ርግጫና ፍጥጫ
የብሎገር ጸሐፍት ታታሪዎች እንዲሁም የድምጻችን ይሰማ የካሜራ ታታሪ ሴት እህታችንም ጨምሮ ሊበረታቱ፣ ሊደነቁ፣ ሊደገፉ፣ ሊሸለሙ ሲገባቸው፤ በተመሳሳይ ሁኔታ የደረሰባቸው ፍዳና መከራ ነው። በጥቅሉ ዕለቱን ኢትዮጵያ ላይ ሲታሰብ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘር ተከል ጨለማዊ አገዛዝ ተወግዶ፤ በልቡ የታበዬው ገዢ ፓርቲ ተወግዶ፤ አቅማችን – ችሎታችን፤ ሊደመጥ የሚችልበት ሥርዓትን መናፈቅ፤ ለናፍቆት „በቃንን” ማስታጠቅ አንገብጋቢው መስመራችን ሊሆን ይገባል።
በተረፈ „በድምጻችን ይሰማ” ያለው ጉልበታም እንቅስቃሴ ሆነ ጉልህ ድንቅ የሴቶች ተሳትፎ ለዛላቂ የነፃነት ትግል ከሚደረገው ጋር አቀናጅቶ የሴቶችን ሰማያዊ ሚስጢር ኢትዮጵያ ላይ ጥቅም ላይ ለመዋል – እንትጋ። እግዚአብሄር አምላክ ለአፈራችን ያብቃን አሜን! እግዚአብሄር ይስጥልኝ ዘሃበሻ ማህበራዊ ድህረ ገጽ። ለሰጣችሁኝ የማያልቅ ጣፋጭ የብዕር እኩልነት ነፃነት ምልክቴ ናችሁ – ኑሩልኝ። አድማጪዎቼም – ኑሩልኝ!
