1. አንድነት ፓርቲ ለሁለት ተሰንጥቋል፡፡ አንደኛው ቡድን በበላይ ፍቃዱ ሁለተኛው ደግሞ በትዕግስቱ አወል ይመራል፡፡
2. እነዚህ ሁለት ቡድኖች በየግላቸው /አንዱ በሆቴል አንዱ በፅ/ቤት/ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደናል በማለት ፕሬዝዳንት መርጠው ነበር..
3. ምርጫ ቦርድ ‹‹በተናጠል ሳይሆን በጋራ ጉባዔ አካሂዳችሁ ፓርቲውን እንደስሙ አንድ አድርጉ፤ ሁለት ሳይሆን አንድ ፕሬዝዳንት መርጣችሁ አሳውቁኝ›› በማለት ለሁለቱም እውቅና ሳይሰጥ ችግራቸውን የሚፈቱበት ቀን ቆርጦላቸዋል፡፡
4. በበላይ ፍቃዱ የሚመራው ቡድን ይህን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ አልቀበልም፤ እንዲያውም ውሳኔውን በመቃወም ሰልፍ እወጣለሁ በሚል ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ ለሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ የመጣልኝ ደብዳቤ መያዝ የሚገባውን ነጥቦች ባለማካተቱ ሰልፉን እውቅና አልሰጠሁትም ብሏል፡፡ በትዕግስቱ አወል የሚመራው ቡድንም ይህ ሰልፍ ህጋዊ ስላልሆነ መፈቀድ የለበትም ሲል አቤቱታውን አቅርቧል፡፡
5. በአቶ ትዕግስቱ የሚመራው ቡድን ችግራችንን ቁጭ ብለን እንፍታ ብልም ሰሚ ስላላገኘሁ በተናጠል ጉባኤውን ዳግም ለመጥራት ተገድጃለሁ ባይ ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ ይህ ዜናም የትዕግስቱ አወል ቡድንን ጉባኤ ይመለከታል፡፡ አሁን ወደ ዝርዝሩ አልፋለሁ፡፡
በአቶ ትዕግስቱ አወል የሚመራው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አካሄደ፡፡
በአቶ ትዕግስቱ የሚመራው የአንድነት ፓርቲ ክፋይ ዛሬ በቶፕ ቪው ሆቴል ባደረገው ስብሰባ መገኘት ከሚገባቸው 239 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ውስጥ 193 ያክሉ ስለተገኙልኝና ይህም በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችል በመሆኑ ስብሰባውን አካሂጃለሁ ብሏል፡፡
ሶስት የፓርቲው አባላት ማለትም አቶ ትዕግስቱ አወል፤ አቶ ጋሻው አሰፋና አቶ ደረጄ ሚሊዮን ለፓርቲው ፕሬዝዳንትነት በእጩነት ቀርበዋል፡፡ ከአዳማ የፓርቲውን ቅርንጫፍ በመወከል የተገኙት አቶ ጋሻው አሰፋ ከውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን ሁለቱ እጩዎች በሚስጥር በተካሄደ የድምፅ አሰጣጥ ተወዳድረዋል፡፡
አቶ ትዕግስቱ አወል ከተሰጠው ድምፅ 136 ሲያገኙ አቶ ደረጄ ሚሊዮን ደግሞ 48 ድምፅ በማግኘታቸው አቶ ትዕግስቱ ፓርቲውን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ዳግመኛ ተመርጠዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው ለኦዲትና ኢንስፔክሽን የቀረቡለትን 10 እጩዎች አወዳድሮ 7 አባላትን መርጧል፡፡ በተመሳሳይ ለብሔራዊ ም/ቤት አባልነት 57 ዕጩዎች ቀርበውለት በ55ቱ ላይ ድምፅ ሰጥቷል፡፡
ለብሔራዊ ም/ቤት አባልነት ከታጩት ውስጥ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙት ሀብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሺ ይገኛሉ፡፡ አመራሮቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እነዚህ የፓርቲያችን አባሎች ከእስር ሲፈቱ ቦታውን ይይዛሉ ብለዋል፡፡
መረጃውን ላደረስከኝ ወዳጄ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ጉባኤ ላይ ተወካዩን አልላከም፡፡ ምክንያቱም ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ ሁለቱም አካሎች በጋራ ጉባዔ እንዲያካሂዱ በመሆኑና ይህ ስላልተፈፀመ በመሆኑ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል፡፡
