የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ” በተመለከተ አሜሪካ ውስጥ ላለፉት ስድስት ወራት ጥናት ሲያደርጉ ቆይተው በቅርቡ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል…
ዶ/ር መረራ ጉዲና፡- ምንም ጥያቄ የለውም፤ ከዳያስፖራው ጋር በሁለት ነገሮች ላይ መግባባት ያስፈልገናል፡፡ እንደሚታወቀው ያለ ዳያስፖራው ድጋፍ መንቀሳቀስ ይከብዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው የፖለቲካ ምህዳር፣ ከሃገር ውስጥ የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ የዳያስፖራው ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ ዳያስፖራው ግን ድጋፉን ሲሰጠን ውሃ ልኩን ካላወቀ፣ ሃገር ውስጥ የሚደረገው ትግል መልኩን ሊስት ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ሰላማዊና ህጋዊ ትግል፣ ዳያስፖራው በውጪ ደረጃና ሚዛን ካየው እንዲሁም እንደዚያ ተንቀሳቀሱ ካለ፣ አገር ውስጥ በዚያ ደረጃ መንቀሳቀስ ስለማይቻል፣ ብዙ ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ ይከሰታል፡፡ ይሄንንም በጥናቴ ተመልክቻለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ ዳያስፖራው በሚሰጠው ድጋፍ መጠን በሚፈልገው አቅጣጫ ግፋበት የማለት ዝንባሌ ይታያል፤ እሱም ያስቸግራል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አስቸጋሪው ዳያስፖራው በተለይ በብሄር የመከፋፈሉ ነገር ነው፡፡ በብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ ዙርያ ዳያስፖራው ሃገር ውስጥ ካለነው በበለጠ ተከፋፍሏል፡፡ ምን ዓይነት ዲሞክራሲያዊ ለውጥ መምጣት አለበት በሚለው ላይ ሀገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎችም ሆኑ ዳያስፖራው ስምምነት ላይ ካልደረሱ፣ ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ወደፊት ለመግፋት ይቸግራል፡፡ በዳያስፖራው እና በሃገር ውስጥ ባለው ተቃዋሚ መካከል ኢትዮጵያ እንዴት ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ትሂድ በሚለው ላይ መግባባት መፍጠር ያሻል፡፡
