«ኤዲያ፤ ሰማያዊ ፓርቲ ቤት የተነሳውን እሳት እንደምንም ብለን ስናደፋፍነው አሁን ደግሞ አንድነት ፓርቲ ቤት ሌላ እሳት ተነሳ ….እርስ በርስ እየተጠዛጠዙ ፌስቡክን አጨናነቁት እኮ፡፡ ምናለ ዙከምበርግ ልክ የውስጥ ስልክ መስመር ወይም የውስጥ ሚሞ እንዳለ ሁሉ ለውስጥ ጉዳይ ብቻ የሚሆን ሌላ የፌስቡክ አይነት ቢፈጥርላቸው….
ይሄን የጻፉት ከበደ ካሳ የሚባሉ የአገዛዙ ካድሬ ናቸው። የመኢአድ እና የአንድነት ዉህድ ፓርቲ ሊቀመንበር ለመሆን፣ በአንድነት በኩል የቀረቡ እጩ ተወዳዳሪዎችና ደጋፊዎቻቸው በግልጽ የሚያደርጉትን ቅስቀሳ ፣ እንደ «እሳት» በመቁጠር ሊያጣጥሉት ሞክረዋል። አዎን እሳት ነው የተነሳው። የሚያጠፋና የሚያቃጥል ሳይሆን፣ የሚያበስል፣የሚያነጠር፣ የሚያሳምር እሳት።
አቶ ከበደ ካሳ፣ ኢሕአዴግ ፕሮፖጋንዳዉ ለመርዛት፣ በተቃዋሚዎች አካባቢ ያሉ መረጃዎች ለመሰብሰ፣ በተቃዋሚዎች ላይ መሰረት የሌለዉን ክስ ለማቅረብ ተቀጥረው የሚሰሩ ጋዜጠኛ ቢጤ ካድሬ መሆናቸው፣ የሳይበር ስፔሱ አለም የሚያውቀው ነው። አቶ ከበደ ለጻፉት ቅልብጭ ያሉ መልሶችም ተሰጥተዋል።
አቶ በላይ በፍቃዱ፣ የአንድነት እጩ እንዲሆኑ ከሚቀሰቅሱት የአንድነት አባልና ደጋፊ አንዱ፣ ወጣት ዳዊት ሰለሞን ነው። ለአቶ ከበደ ሲመል እንዲህ ሲል ጽፏል፡
« ከቤ ምን ይደረግ፣ ፓርቲዎቹ ቤት ሀሳብን በነጻነት መግለጽ የሚባል መብት አለ፡፡ ችግሩ እናንተ ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ኒዎ ሊበራሎች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ህገ ወጥ ነጋዴዎች፣ ወዘተ ሲሉ፣ 40 ብር አበል ተከፍሏት፣ ስብሰባ የገባች የቀበሌ ተስፈኛ ጭምር፣ ሰዉዬው የተናገሩበትን የድምጽ ቃና ሳትለውጥ፣ እንደ ገደል ማሚቶ ማስተጋባቷ ነው። ከቤ ሙት፣ እስኪ አስበው፣ ፓርላማውን የተቆጣጠሩት ተቃዋሚዎች ብቻ ቢሆኑ፣ እንደዛሬው ፓርላማ ጭብጨባ ብቻ የሚሰማበት ይመስልሃል? እኔ ግን አይመስለኝም፡፡ እና… ጋዜጠኛም አይደለህ። ሰዎች ሀሳባቸውን ልዩነታቸውን እያወጡ እንዲጽፉና እንዲነጋገሩ ለማበረታታት ሞክር፡፡ ረስቼው አንተም ለካ ያው የተሰጠህን የምትጽፍና የተሰፈረልህን ብቻ የምታስብ ነህ»
ወጣት ዳዊት ሰለሞን የሚደግፈውን አቶ በላይን የሚቃወሙና፣ የአሁኑ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው እንዲመረጡ በጣም ከሚቀሰቅሱትና ከሚጽፉት መካከል ደግሞ፣ የአንድነት ከፍተኛ አመራርና የዉጭ ጉዳይ ሃላፊው ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ናቸው። ኢንጂነሩ እንዲህ ነበር ያሉት፡
« አቶ ከበደ አንድነት ቤት እሳት ተነሰቷል የሚል ሰጋት እንዳደረባቸው ለመጻፍ ሞከረዋል። ያው ሰው የመሰለውን የመናገር መበቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሆኖም በተለያዬ መጣጠፎች የማውቃቸው አቶ ከበደ፣ በዚሀ በፌስ ቡከ የሚጻፉ መልከቶችን እንደ እሳት መቁጠራቸው ግን ለኔ አልገባኝም፡፡ ይህ እኮ አንዱ የዴሞክራሲ ባህል ነው፡፡ ይህንን በፌስ ቡክ የሚጻጻፉት ልጆች፣ ቁርስ ምሳ እራት አብረው ነው የሚበሉት፡፡ ሌላው አቶ ከበደ ቢችሉና በእኛ የምክር ቤት ስብሰባ ተገኘተው የሚንጸባረቀውን የሀሳብ ልዩነት በተመለከቱ ኖሮ። ይችን የሀሳብ ልዩነት እንደ ትልቅ ነገር ባልቆጠሩትም ነበር፡፡ እኛ እኮ የምንታገለው የሀሳብ ልዩነት እንዲኖር ነው»
ሌላው ለአቶ ከበደ ምላሽ የሰጡት «ባን ቤጋል ኢትዮጵያ»፣ በሚል ስም የሚጦምሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡
«እርግጥ ነው፣ በነአቶ ከበደ ቤት፣ የሀሳብ ልዩነት ማንፀባረቅ መዘዙ ከበድ ያለ መስዋትነት ስለሆነ፣ ማንኛው የአቶ ከበደ ይሄን ብሉ ሲባሉ ይበላሉ፣ ሽኑ ሲባሉ ይሸናሉ፣ ስማችሁን ቀይሩ ሲባሉ ይቀይራሉ፣ ስለዚህ በመንፈስ ሁሌም አንድ ሀሳብ አንድ ልብ ናቸው። ዴሞክራሲም ለነሱ ይህ ነው። የእንግሊዝ የፓርላማ አባላት የሀሳብ ልዩነት በማንፀባረቅ በስሜት ሲጨቃጨቁ ፣ ለነከቤ ስነ ምግባር አልባነት ነው። የፓርላማ አባላት፣ እጅ አውጡ ሲባሉ እጅ ማውጣት ነው ። ይህ በአንድነት ዉስጥ የሚታየው ለነከቤ ጥሩ የዴሞክራሲ ባህል ያስተምራቸዋል»
እንግዲህ ልዩነቱ ይሄ ነው። ኢሕአዴግ ዉስጥ መሆን ለጊዜው ጥቅም ይኖረዋል። ግን ትንሽ ከመስመር ዝንፍ ከተባለ አለቀ ነገሩ። አንድ ጊዜ አንድ ጓደኛዬ ትሩ ደሞዝ ነበረው። ያለው ይበቃው ነበር። እድገት ፍለጋ የኢሕአዴግ አባል ሆነ። እንደተመኘውም ተሳካለት። እኛ ተዉ ብለን መክረነው ነበር። አለሰማንም። አንድ ወቅትማ «ዝም ብላችሁ ነው እናንተ » እያለ የተነፋዉን የልማት ወሬ ማውራት ጀመረ። ብዙም አልቆየም ከሥራው ተባረረ። የኢሕአዴግ አባል በመሆኑ ፣ ከድርጅቱ የሚሰጠው ት እዛዝ አለ። በነርሱ አሰራር አንድ የኢሕአዴግ አባል ምንም ይሁን ምንም የተባለው ት እዛዝ መቀበል አለበት። የድርጅቱ ዉሳኔ እንደ ቃለ-እግዜር መከበር አለበት። ያዘዙት ከባድ ነገር ነበር። እኛን ለኢሕአዴግ አባልነት እንዲመለምል። ለካ አጅሬ ቱሪናፋ ሲነዛብን የነበረው ታዞ ኖሯል። ያዘዙትን ባለማድረጉ፣ በግምገማ አፈር ድሜ ገባ። ያገኘዉን እድገት መቀማት ብቻ ሳይሆን፣ ጭራሹኑ ከስራው አባረሩት። አይ ጭካኔ !!! እንግዲህ እንዲህ ናቸው እነርሱ ! ርህራሄ የላቸውም ! ፉክክር፣ ነጻ ዉይይት፣ ዲሞክራሲ ..ብሎ ነገር የለም። ለነርሱ ሁሉም ነገር ወይ ጥቁር ፣ ወይም ነጭ ነው።፡ ለነርሱ ወይ የደርጅቱን ት እዛዝ የምንቀበል ወዳጅ ነን ወይም ጠላት ነን።
አቶ ከበደ እዚህ ማጥ ዉስጥ ነው ያሉት። እኛ ብንቃወም ብዙም ችግር የለዉም። እርሳቸው ስራቸውን ካልሰሩ፣ ወይንም ትንሽ ቅሬታ ኢሕአዴግ ላይ ካቀረቡ አለቀላቸው። ስለዚህ ብዙም አልፈርድባቸዉም።
