Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” (ጥናታዊ ጽሑፍ – በጌታቸው ረዳ)

$
0
0

በካሊፎረኒያ ስቴት በሳን ሆዘ ከተማ በሃያት ሪጀንሲ ሳንታክላራ ሆቴል በሰኔ 26/2006 (July 3/2014) በሞረሽ ወገኔ የአማራ ሲቪክ ማሕበር በተዘጋጀው ሕዝባዊ ስብሰባ በአቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ..

Getachew-Reda-a

የተከበራችሁ የመድረኩ አዘጋጆች እኔን ከእነዚህ የታወቁ ዓለም አቀፍ ምሁራን ጋር ሆኜ አገራችን በአሁኑ ሰዓት ስለ አለችበት ሁኔታ ለመነጋጋር ስለጋበዛችሁኝ፤ ምስጋናዬ የላቀ ነው። አመሰግናለሁ።

እንዲሁም እናንተ ክቡራን እና ክቡራት ኢትዮጵያዊያን ወንድሞች እና እህቶች፤ ስለ አገራችን ጉዳይ ከእኛ ጋር ለመወያየት በመምጣታችሁ እጅግ አማሰግናለሁ።

ከሁሉም አስቀድሜ አንድ ነጥብ ለማስረገጥ የምፈልገው ጉዳይ፤ በዚህ ስብሰባ በእንግድነት ስጋበዝ፤ የምሰነዝራቸው አስተያየቶች እና ትችቶች ማንም የፖለቲካ ቡድን ወይንም ድርጅት ወክዬ ሳይሆን እራሴን አንደ የኢትዮጵያን ሰማይ ድረግጽ አዘጋጅነቴ እንደ ጌታቸው ረዳ በግል የሚወክል ነው። ማንም ተቃዋሚ ወይንም ሚዲያ በምሰነዝረው አስተያየት የመከራከር የመተቸት መብቱ የተጠበቀ ነው። ከዚህ በታች የማቀርበው ጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋት የልተመረመረ ታሪክ በኔ በትግራያዊ ነገድ በኢትዮጵያዊ ዜጋ ተደረገ የመጀመሪያ ጥናት ስለሆነ፤ የታሪክ ምሁራን ለምርምር ሊጠቀሙበት ፈቅጃለሁ።

ይህ ካልኩኝ፤ ወደ ውይይታችን ልግባ።

ከናንተው ጋር ለመወያየት መርጫቸው የነበሩ ሁለት ርዕሶች ነበሩ። ሆኖም ሁለቱን ርዕሶችን አንስቼ ለመወያየት ከጊዜ አንጻር ማብቃቃት ስላለብኝ፤ በአንደኛው ርዕስ ብቻ በማትኰር ከናንተው ጋር እወያያለሁ።

አሁን በመረጥኩት ርዕስ እና ከአዘጋጆቹ ተጠይቄ መልስ አንድሰጥበት ያዘጋጀሁትን “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” በሚል ጉዳይ አንስቼ ከናንተው ጋር እወያያለሁ። ትንታኔዎቼም አሁን ላለው ውዥምብር መሰረታዊ “ግንዛቤዎች” እንዲኖሩን ይረዱናል።

ወደ ዝርዝር ንግግሬ ከመግባቴ በፊት፤ አንድ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ። የመድረኩ አዘጋጆች ቀደም ብለው እንደገለጹት የጎሳ ትውልዴ ትግራይ ውስጥ ነው። ወያኔ የኔን ፖለቲካዊ ክርክር ለማፍረስ እንዲመቸው ማንነቴን እያወቀም ቢሆን “ትግሬ” አይደለም፡ በማለት የኔን ትግሬነት ለመንጠቅ በተከታዮቹ በኩል በየኢንተርኔቱ ማንነቴን ለመንጠቅ ያልጐለጐለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የለም። ትግሬ ሆኖ ከአማራ ወይንም ከአገው ‘ነገድ’ ያልተዋለደ ወይንም ከሌሎች ነገዶች ያልተዋለደ ኢትዮጵያዊ የለም። ሁላችንም ተሳስረናል። በተለይም ትግሬ ሆኖ የገዛ ስሙ ወይንም የወላጆቹ እና የአያቶቹ ወይንም የቅድመ አያቶቹ ስም “የአማራ ስም” የሌለው ትግሬ በምንም መልኩ አይገኝም። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ብሔረተኛ መሳፍንቶች ‘አማርኛም’ የትግሬዎች አይደለም በማለት አፄ ዮሐንስንም ጭምር ለማሳመን ተከራክረው “ተቀባይነት እንዳጡ’ የትግራይ ታሪክ ፀሐፊዎች ነግረውናል። የተባለው ቋንቋ በትግሬ ነገሥታቶች እና የትግሬ የጥንት ሊቃውንት ከትግርኛ ቋንቋ ይልቅ ከጥንት ጀምሮ በግዕዝ እና በአማርኛ መገናኛቸው ለምን አድርገው እንደመረጡትም ለታሪክና ለነገድ ተመራማሪዎች እተወዋለሁ።

ስለ እኔ ማንነት ይህ ካልኩኝ በኋላ። ትግሬ ሆኖ “ወያኔን የሚቃወም የለም” የሚል ወያኔዎችም ሆኑ ወያኔንም በሚቃወሙ ጭምር ይህ እምነት ስላለ ነው ይህንን ለመግለጽ የፈለግኩት። ትግሬዎች ለወያኔ ካለቸው ድጋፍ እና ብዛት አንፃር ስንመለከት ነገሩ እውነትነት አለው። ለዚህም ነው፤ አንድ ታዋቂ ጸሐፊ ክርክርህ ስመለከት እውነት ከትግሬ ነው የበቀለው ስለምል “እውነት ከትግራይ ትውልድ አለህ?” ብለው በኢመይል የጠየቁኝ አንድ ታዋቂ ጸሐፊ ኣሉ፡፡ አንድ የወያኔ ብሔረተኛም ‘እውነት ትግሬ መሆንህን ታምናለህ? እንዲህ ያለ ግልጽ ትግሬ አይተን አናውቅም” በማለት ግትር እውነታየን አስገርሞታል።

የማከብረው ወዳጄ ዶ/አሰፋ ነጋሽም ያንተን ትግል ስመለከት “እስራላዊው ጋዜጠኛ “ገዴዎን ለቪ” ሆነህ ትታየኛለህ። ብሎኛል። ገዴዎን ለቪ ለማታውቁት ሰዎች፤ ገዴዎን ለቪ እስራኤላዊ ነው። እስራኤል የፓለስታይን ስቃይ ማቆም አለባት ብሎ የእስራልን ወንጀል ከሚያጋልጡ ታዋቂ ጋዜጠኛ እና ሰብአዊ ጠበቃ ነው። ወያኔዎች እኔን እና መሰል ጓደኞቼን ትግሬነታቸው የከዱ ብለው “ሽዋውያን ተጋሩ” እያሉ አንደሚጠሩን ሁሉ በእስራሎችም ገዴዎንን “ሓማሳዊ ፕሮፓጋንዲሰት” (propagandist for the Hamas) የሚል ቅጥያ ተሰጥቶታል። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ገዴዎንን “እስራላዊ አርበኛ” ብለው ይጠሩታል። በዚህም የ2012 የኢንተርናሺናል ሚዲያ አዋርድ ተሸላሚ ሆኗል። ትግሬዎች የጐንደሬዎች እና የወሎዎችን መሬት በጉልበት ቀምተው መኖርያቸው አንዳደረጉት ሁሉ፤ ገዴዎንም እስራሎችን የፓለስቲኒያን ‘ዌስት ባንክ’ መሬት ቀምተው ለሰፋሪ እስራሎች በመስጠታቸው፤ እዛው እየሰፈሩ ያሉት የእስራል ሰፋሪዎችም፤ “society’s of Moral Blindness” “የሞራል እውራን ማሕበረሰብ” ሲላቸው፤ የፓለስቲኒያን መሬት ነጥቆ የመኖርያ ህንፃ በመገንባት ለእስራሎች መኖሪያ ያደረገው የንጥቂያ ወንጀልም፤ the most criminal enterprise in ( Israel’s ) history ብሎታል። በዚህ ምክንያት ገዴዎን ለቪ ከእስራል ወገኖቹ ብዙ የዘለፋ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶበታል። ብዙ መገለልም ደርሶበታል።

ወደ እኛው ታሪክ ስመልሳችሁ ደግሞ ብዙ ገዴዎኖች ባንኖርም፤ ወያኔን የምንቃወም ትግሬዎች ጥቂት መሆናችን እርግጥ ነው (ብዙ የቀራቸው መንገድ ቢኖርም አሁን አሁን የኔን ኮቴ ተከትለው የመጡ ጥቂቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።) አየተሰደብኩም ሆነ ከሕብረተሰቡ አንድነጠል እየተደረገም ቢሆን እዚህ ድረስ ተጉዤ አሁን በርካታ ተከታዮች በማፍራቴ ኩራት ይሰማኛል። ወዳጄ ገብረመድህን እንዳለው “ባንተ ኮቴ ተከትለን እዚህ አንድንደርስ ያደረግከው የትግል አርአያ በትግራይ/የኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ ለወደፊቱ ይጻፋል።” ብሎ የጻፈልኝ የግል ደብዳቤ ሳስታውስ በትግሉ እንድቀጥል አበራታች ሆኖኛል።

ወያኔ ትግራይ በ1983 ዓ.ም ስልጣን ከያዘ በሗላ፤ ጥቃቱ ያነጣጠረው “እንደ ሕብረተሰብ” በአማራ ሕብረተሰብ ላይ እና “እንደ አገር” በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ አንደሆነ ሃቅ ነው። በአማራ ላይ የደረሰው ጥቃት እዚህ ያሉ ክቡራን ሊቃውንቶች ስለገለጹት ወደ ዝርዝር ጥቃቱ አልገባም። ነገር ግን የትግራይ ብሔረተኞች በዚህ ሕብረተሰብ ላይ ጥቃቱን ለማነጣጠር ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድ ነው? የሚለው ግን ለማብራራት እሞክራለሁ።

ትግራይ ብሔረተኞች የአማራ ጥላቻቸው ከሌሎች ጎሳዎች ይልቅ ለምንድነው የበረታው? የሚለው መመለስ አለብኝ? ይህ ብቻ ሳይሆን “የትግራይ ብሔረተኛ ስሜት” መመንጨት የጀመረው መቸ ነው? የሚለውም አብረን ከመለስን ለጥላቻው መንስኤ ምዕራፉ ከየት አንደጀመረ ለመረዳት ይረዳናል።

የትግራይ ብሔረተኛነት ስሜት መታየት የጀመረው የትግራይ መሳፍንቶች እርስበርሳቸው ለስልጣን ሲሉ የአንድ አውራጃ ሕዝብ ከሌላው አውራጃ ጋር በደም፤ በአጥንት፤ በሃብት እና በሰራዊት ብዛት እየተኩራሩ በላቀ ተወልጄነት ወይንም “ትግሬነት” በመናናቅ ‘አውራጃዊ ስሜት’ በሕዝቡ ስሜት ላይ እንዲታነፅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለስልጣን ሲሉም የአንድ እናት ወይንም የአጎት ልጆች እርስ በርሳቸው እስከመገዳደልም ደርሰዋል።

ይህ የበላይነት እና አውራጃዊ ስሜት አክሱሞች በዓድዋዎች ዓድዋዎች በአክሱሞች፤ አንደርታዎች እና ዓጋሜዎች በመላ የትግሬ እና ኤርትራ ተወልጄ ገዢዎች ላይ የበላይነት ለማረጋጋጥ ሲሉ አውራጃዊ ስሜት እንዲስፋፋ አድርገዋል።

ይህ የእርስ በርስ አከባቢያዊ የመናናቅ ስሜት እንዳለ ሆኖ፤ ከሸዋ ወይንም ከጐንደር፤ ከወሎ ወይንም ከሌላው አካባቢ አዲስ ገዢ/ጉልበተኛ ሲነሳባቸው ግን ‘አውራጃዊ የመከፋፋል ስሜታቸውን ወደ ጎን በማቆየት” ሁሉም ባንድነት “የትግሬ ብሔረተኛነት ስሜት” በማሰባሰብ እንደ ባዕድ በሚመለከታቸው የሌሎች አካባቢ ነገሥታት/ጉልበተኞች ላይ ያምጻሉ። የንጉሡ ስም ካልተሳሳትኩ በአጼ አምደጽዮን ጊዜ ይመስለኛል……… በገዢነት ወደ እንደርታ በመጡበት ጊዜ () ትግራይ ውስጥ ከተወልጀዎች ውጭ የሆኑ ከድሃ መደብ ቤተሰብ የተገኙ ትግሬዎች ወይንም ከሌላ አካባቢ የመጡ በንጉሡ ስለተሾሙ “ሓለስተይቶት” አይገዙንም በማለት ጠባብ የትግራዋይነት ስሜት አንጸባርቀዋል። ሓለስተይቶት ማለት “የበታቾቻችን/ዲቃላዎች” ወይንም በአሜሪካኖቹ አሰያየም “ኔገር” አይገዛንም አንደማለት ይመስለኛል። ዛሬ የምትሰሙዋቸው አንዳንድ የወያኔ ሰዎችም ሆኑ ኤርትራዊያኖች እርስ በርሳቸው ሲነታረኩ/ሲጣሉ/ሲከፋፈሉ “እዚኦም ባ ል መንዮም!?” (እነዚህ እነማን ይባላሉ?!) በመባባል አርስበርሳቸው በመናናቅ የሚያሰምዋቸው ቃላቶች ከዚያ ዘመን የወረሱዋቸው ትምክህታዊ ባህሪያቶች ናቸው። ለምሳሌ የወያኔው ብስራት አማረ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ‘ቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ’ አንደወረደ፤ በጸጥታ መ/ቤት ሐላፊዎች ትዕዛዝ “ወደ አገር አንዳይገባ” ታግዶ ወደ መጣበት አሜሪካ አንደተመለሰ ከታወቀ በሗላ ‘ገዛ ተጋሩ’ በሚባል አፍቃሬ የወያኔ ‘ፓል ቶክ’ መድረክ ስለሁኔታው ተጠይቆ ሲያብራራ፤ የተጠቀመበት ቃል ያንኑ ቃል ነበር። “እነዚያ ዲቃላቆች” ነበር ያላቸው።

ያም ሆነ ይህ፤ ከሌላ አካባቢ የመጡ ሹመኞች በግማሽ የተወለዱ ትግሬ ገዢዎችን ‘ዲቃላዎች’ ወይንም ‘ባዕዳን’ ወይንም “ሓለስተይቶት” አይገዙንም በማለት ጠባብ የትግራዋይነት ስሜት አንጸባርቀዋል።

ያም ሖኖ በሌሎቹ አከባቢ ጉልበተኞች ቢገዙም ስሜታቸውን ‘በማመቅ’ አንዳንዴም ‘በማመጽ’ እስከ አጼ ዮሐንስ ድረስ ቆይተዋል። አጼ ዮሐንስ በነገሱበት ወቅት ግን የትግሬ ሕዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ ተገዝቶላቸዋል። እስካሁን ድረስም የልጅ ልጆቻቸውን “ደቂ ላሕምና” (የላሜ ቦራ/ የላማችን ልጆች” እያሉ ይጠሯቸዋል።ለምሳሌ የትግራይ

ሕዝብ በደረግ ጊዜ “ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን “ወዲ ላሕምና” አናስጠቃም በማለት ስለጮኸ ደርግ እርምጃ ከመውሰድ ተገ’ዶ ነበር።
ዮሐንስ ከሞቱ በሗላ ዘውዱ በምኒልክ ሲተካ፤ ትግሬዎች ከፍተኛ የሆነ “የባዶነት ስሜት” ወይንም ‘emptiness’/ a sense of generalized boredom) ተሰምቷቸዋል። የባዶነት ስሜት ለምን ሊሰማቸው ቻለ?

የትግሬ ሕዝብ ለዘመናት በራሱ አስተዳዳሪዎች የመገዛት ልምድ ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የቆየ ስለሆነ፤ የካባቢው ሕዝብ ምንም ኩፉ ስርዓት እና ጨካኝ ገዢ ቢሆንም በአካባቢ ገዢ የመገዛት ፍላጎታቸው የበረታ ነው። ለዚህም ልዩ ምክንያት አለው። ምክንያቱም ስልጣን የያዘው ሕዝቡ ሳይሆን ገዚዎቹ ቢሆኑም “ስልጣን የያዙ ገዢዎች ትግሬዎች ከሆኑ፤ የትግራዋይነት ጉልበት እና የበላይነት ስሜትን በስነ ልቦናቸው እንዲቀረጽ በማድረግ በሌሎች ጐሳ ገዢ መደቦች ላይም ሆነ በሌሎች ጐሳዎች ላይ የበላይነት ስሜት አንዲያድርባቸው ሆኗል።”

እንግዲህ ከዚህ በመነሳት የትግራዋይነት ስሜት ከዘመነ አክሱም ጀምሮ እየተገነባ የመጣው የበላይነት እና የጉልበተኛነት ስሜት በሕዝቡ ስሜት በመቀረጹ ከትግሬ ሌላ ገዢ ካስተዳደራቸው፤ ጉልበታማነታችን እና እንዲሁም የትግሬነት የበላይነት ክብራችን ‘ተነጠቀ’ በሚል ስሜት በመነሳሳት የሌላው ጐሳ ንጉሥ በባዕድነት በመመልከት “ገዢዎች ኖረን ተገዢዎች አንሆንም” በሚል ስሜት “እሩቅ ትዝታ” ውስጥ በመግባት የስልጣን መለዋወጡ ጉዳይ ተፈጥሮአዊ መሆኑን ላለመቀበል ‘የተጠቂነት ስሜት’ አድሮባቸው ‘አንገዛም’ በማለት ጦርነት እና ግጭት ይፈጥራሉ። ጦርነቱ እና ግጭቱ በዛው ሳይወሰን፤ “ረዢም እና ጥልቅ የጥላቻ አጥር” በመገንባት ረዢም የሚጓዝ፤ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ የጥላቻ ውርስ ‘የማስተላለፍ ባሕል’ እያስረከቡ አልፈዋል።

ስለሆነም ነው የትግሬ ብሔረተኞች አጼ ዮሓንስ በመተማ ጦርነት ከተሰው በሗላ፤ ተከትለው የዙፋኑን መንበር የተረከቡት የሸዋው ንጉሠ ነገሥት “ምኒልክን” አንደጠላት እና ባዕድ ንጉሥ አድርገው በመመልከት፤ የትግሬ ሥልጣን ‘ወደ ሸዋ ተዛወረ’ በሚል ቁጭት የተነሱት የዘመኑ መሳፍንቶች ከንጉሥ ምኒልክ ጋር አለመጣጣም ፈጥረው “በሸዋ አንገዛም” በማለት ንትርኩ ወደ ሕዝቡ ተላልፎ መለስተኛ ጦርነት በትግራይ አካባቢ ተካሂዷል። ያ ዘመን፤ የትግሬ ብሔረተኞች በቁጭት የምኒልክን ዘመን “ዘመነ ሸ” ወይንም “ዘመነ ሸዌ” በማለት ይጠሩታል።

በትግሬ ብሔረተኞች ጸሓፊዎች መሰረት፤ ‘የሸዋ እና የትግሬ መቃቃር’ “ዘመነ ሸ” የሚሉት በንጉሥ ምኒልክ ዘመን ብቻ ሳይወሰኑ የትግሬ ብሔረተኛነት በሸዋ ነገሥታት እና በትግሬ ገዢዎች ቅራኔ የተፈጠረበት ዘመን ወደ ሗላ በመጎተት ታሪካዊ እና መሰረታዊ ቅራኔዎቻችን መነሻዎች ከሚሏቸው ነጥቦች ውስጥ አንዲህ ይገልጹታል።
የማነ ገብረመስቀል፤ የተባለው “ቀዳማይ ወያነ” የሚል መጽሐፍ የጻፈ ጸሐፊ በትግርኛ አንዲህ ይላል፦

“የትግሬ ሕዝብ ብረት አንስቶ ለመታገል የተገደደበት ለቀዳማይ ወያኔ አመጽ መነሻ በወቅቱ በተከሰቱ ምክንያቶች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፤ ለዘመናት መፍትሄ ሳያገኙ በሕዝቡ “የልቦና ግምጃ ቤት” መሽገው የነበሩ “ታሪካዊ እና መሰረታዊ” ምክንያቶችም ጭምር ነው።”

ዶ/ር ክንፈ አብርሃም የተባለ ሌላው የትግሬ ምሁር (ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል) እነኚህ የሚከተሉት ምክንያቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የትግራይ ሕዝብ በሸዋ ገዢ መደቦች ላይ “ጥላቻ” አሳድሮ ነፍጥ አንሰቶ ሊታገላቸው ትልቅ ምክንያት ሆኖታል የሚላቸው ምክንያቶች እንዲህ ይዘረዝራል።

(ሀ) በሥልጣን ሽሚያ ምክንያት የተፈጠረው ፖላቲካዊ ግጭት በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጠረው ስሜት፤ የጀመረው፤-

“ከአክሱም መንግሥት መዳከም ወዲህ፤ እና አንዲሁም ድንግተኛ የሆነ ያልተጠበቀ የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ሞት ተከትሎ የመጣው የሸዋ መንበረ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ “ትግሬዎች በትክክለኛ የፖለቲካ/ሥልጣን ሚዛን ላይ አይደለንም። ሥልጣናችን እና ታሪካችን በሸዋ ገዢ መደቦች ተነጥቀናል።” ክንፈ አብርሃም (2001- Ethiopia from Empire to Federation p.223) የሚል ስሜት አሳድረዋል።

ቀዳማይ ወያነ የሚል መጽሐፍ ደራሲ የማነ ገብረመስቀል ድግሞ እንዲህ ይላል፡-

“የሥልጣን ሥርወ መነግሥት እና ሥልጣኔ ማዕከላዊ መሰረቱ ትግራይ ውስጥ እና በትግሬዎች እጅ እያለ፤ በተንኮል ወደ ሸዋ ተወስዷል፤ ስለሆነም (ትግሬዎች) በሸዋ ገዢዎች ላይ ከፍተኛ ጥላቻን አከማችተዋል። በዚህ ሳይወሰን ቅራኔው ወደኋላ ብንሄድ የሸዋው የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የሆነው “ይኩኖ አምላክ” ሥልጣን ከያዘ በኋላ የእንደርታ (ትግራይ) ገዢ የነበረው ዓብየዝጊ እራሱ የሰለሞን ሥርወ መንግሥት ነኝ ብሎ በሚጠራው “ቡድን” ላይ ዓመፅ አካሄዷል። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ በሸዋዎች ላይ ብዙ ተቃውሞዎች ተቀጣጥለዋል። (የማነ ገብረመስቀል ‘ቀዳማይ ወያነ’ ገጽ 23)

እንግዲህ የትግራይ ብሔረተኞች ከሸዋ ጋር ቅራኔ የፈጠሩት ከይኩኖ አምላክ (12ኛው ምእተ እዝጊ) ዘመን የጀመረ ነው ብለው ነግረውናል።

የማነ ‘ቀዳማይ ወያነ’ በሚባለው የትግርኛ መጽሐፉ በሰፊው የገለጸው ባጭሩ አሳጥሬ ነጥቦቹ ለናንተ ጀሮ እንዲመች ላቅርብ።

እንዲህ ይላል፦

“የአክሱም መዳከም ተከትሎ ትግሬዎች ከተዳከሙ በኋላ፤ ትግርኛ ተናጋሪው ሕዝብ በተለይም ለሁለት ከተከፈለ በኋላ (ኤርትራ እና ትግራይ ማለቱ ነው)፤ ኩፉኛ ተዳክሟል። ትግሬዎች ለመዳከም የመጀመሪያ ተጠያቂዎች አድርጐ የሚያቀርባቸው አነዚያ አፄ ዮሓንስ ከሞቱ በሗላ የመጡ የሸዋ ገዢ መደቦች ናቸው።” ይላል። የማነ ገብረመስቀል።

ይህንን በተመለከተ “ዶ/ር ክንፈ አብርሃምም” እንዲህ ይላል፤-



Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>