ያም ሆነ ይህ እኔና እኔን መሰል ስዎች ያልሆነውን ሆናችሁ ተብለን የምንገፍው የመከራ ህይወት በኢትዮጵያችን የነፃነት ቀን እንዲጠባ የሚረዳ ክሆነ ፤ የሚከፈለው መስዋዕትነት ቢያንስ እንጂ ፈጽሞ አይበዛም:: በትውልድና በታሪክ ፊት ለከበረ ነፃነት ሲባል ዋጋ መክፈል ተመርቆ መፈጠር እንጂ ከቶም አለመታደል አይሆንም:: የልጆቻችንና የሚስቶቻችንም ስብራት ሁላችንም የምንኮራባት ሀገር ስትኖረን ያን ግዜ ይጠግን ይሆናል ::
ዛሬ ግን በዚች ሀገር የፍትህ ስርዓት አለን ብለን መናገር ፈጽሞ የማንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን :: እንደዚህ ዘመን ፍትህ መሬት ላይ ተጥሎ የተዘበተበት ዘመን ይኖር ይሆን ? ፍርድ ቤቶቻችን የፍትህ መባ የሚፈታባቸው ምኩራቦች እስኪሆኑ ድረስ አበክረን ልንታገል ይገባል:: ይኽንን የነፃነት ብርሃን የሚናፍቅ ህዝብ በልበ ሙሉነትም የሚታገል ትውልድ የነፃነቱ ባለቤት ይሆናል:: ለመታግል ገዠዎችን መፍራት አያስፈልግም:: በተላይ ወጣቱ ለነገዋ ሀገሩ ዛሬ በእውነትና በልበ ሙሉነት ይቁምላት :: የኢትዮጵያን ህዝብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከልብ የማይሰራ የኢህአዴግ አመራር ከፕለቲካ ሜዳው በአስቸኳይ ሊወጣ ይገባዋል፤ በተቃዋሚ ጎራውም ይኽን መሰል አስተሳሰብ ያለው ወገን ካለ መንገዱን ይልቀቅ:: ከዚህ በላይ ኢ-ፍትሐዊነትንና ኢ-ሰብአዊነትን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያሰፈኑ ሊቀጥሉ አይችሉም፤ ለፍትህ ለወንድማማችነትና ለነፃነት መንገዱን መልቀቅ አለባቸው:: በእኔ እይታ ሁሉንም የድርድር በሮች ዘግቶ የምላችሁን ብቻ ተቀበሉ ለሚል ጠቅላይ አገዛዝ መታዘዝ በሽታው እንዲብስበት ማድረግ ብቻ ነው :: ዘላቂ መፍትሄው ደግሞ በየግዜው የሚከፈለውን ዋጋ እየከፈሉ ከእውነትና ነፃነት ጋር መቆም ብቻ ነው::
በቃልቲ እስር ቤት የሚገኘው አቶ አንዱዓለም አራጌ ዋለ ” ያልተሄደበት መንገድ ” መጽሐፍ የተወሰደ
