Quantcast
Channel: Ethio Andinet ኢትዮ አንድነት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

ተዋርደን አንቀርም!

$
0
0

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት  (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)
ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰች ያለውን ግፍና በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ፓርቲያችን በወሰነው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀን ነበር። መቼም ህዝባችን በጭቆና ውስጥ ስለኖረ በመብቱና በግዴታው መሀል ያለውን ድንበር በውል ካለመረዳቱ የተነሳ ሰልፉ እንዲደረግ ስለመፈቀዱ በተደጋጋሚ ስንጠየቅ ነበር…..

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር) Eng.Yilkal Getnet Chairman of Blue Party.

ሕጉ የሚለው ግን ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው። በተቃራኒው መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ በዕለቱ ለሰላማዊ ሰልፉ የደህንነት ከለላ መስጠት የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው ሰልፉን ለጠራው አካል ችግሩን ገልጾ ቀኑ እንዲተላለፍለት ይጠይቃል። በመሆኑም ይህን መሰል ጥያቄ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ለፓርቲያችን ባለመቅረቡ በሙሉ ልብ ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ተያያዝን።

ሁሌም ቢሆን መንግሥት ሰበብ ፈልጎ ሊወነጅለንና ከመስመር ሊያስወጣን እንደሚፈልግ በሚገባ እናውቃለንና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ጥንቃቄ እናደርጋለን። ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ባሳወቅን በአስራ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ምላሽ ስላልመጣ ሙሉ በሙሉ ሕጋዊነታችንን አረጋግጠናል ማለት ነው፤ እነሱ ደግሞ ጠብ-መንጃ በእጃቸው አለና የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላሉ።

አቶ ሽመልስ ከማል ለሚዲያዎች የሰጡትን ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላና ሰበብ አዳምጨዋለው። “ሰላማዊ ሰልፉን ያገድንበት ምክንያት ፀረ-ዐረብ መፈክሮች ስለነበሩ ነው” ብለዋል። መጀመሪያ ደረጃ ሰልፉ ገና ከግቢው ፈቅ ሳይል ነው ያፈኑት፣ ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ በአንድ እየሆንን ወደ ሰላማዊ ሰልፉ መዳረሻ ለመሄድ ስንሞክር የተወሰኑ አመራሮችን አራት ኪሎ አካባቢ ያዙን፤ እነሱ ቀድሞውኑ ሰልፉ እንዳይካሄድ ስለወሰኑ ነው እንጅ ትንሽ እንኳ ተንቀሳቅሶ የሰልፉን ባህሪ ለመገምገም ምንም ዕድል አልሰጡንም።

ለምሳሌ ሰልፉን እንደምናደርግ ይፋ ባደረግን ማግስት ከራዲዮ ፋና ተደውሎ አንዳንድ ጥያቄዎች ተጠይቄ ነበር። በቃለ-መጠይቁ ሰላማዊ ሰልፉ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም እንደምናደርግ ተናግረናል። ጋዜጠኛው ለሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መልዕክት ካለ ብሎ በጠየቀኝ ወቅት የሳውዲ ዐረቢያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው ምልክትና ጽሁፍ ኃይማኖትን የሚመለከት በመሆኑ ዜጎች በስሜታዊነት ባንዲራ እንዳያቃጥሉ፣ እነሱ ቢያዋርዱንም እኛ ግን ክብር ያለን ዜጎች ስለሆንን ተቃውሟችንን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እንዳለብን ተናግሬ ነበር። ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በዚህና በተለያየ መንገድ በማያሻማ ሁኔታ መልዕክት ባስተላልፍም እነሱ ግን ይህን በመቁረጥ አላስተላለፉትም። እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ የአቶ ሽመልስ ከማል ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑን ያስገነዝባል።

ሁለተኛ የአንድ ሀገር መንግሥት ዜጎቹ እየተደፈሩ፣ በማጎሪያ ካምፕ በረሀብና በውሃ ጥም፣ ሌላው ቢቀር መጸዳጃ ቤት እንኳ ተከልክለው ፍፁም ከሰውነት ክብራቸው ወርደው እየተበደሉ፣ እየተገደሉ ባለበት ወቅት ገና ለገና ተቃዋሚ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በሚንጸባረቅ ጥላቻና ተቃውሞ የዲፕሎማሲ ግንኙነቴ ይበላሽብኛል ብለን መናገር እንችላለን? ሌላው ይቅር አንድ ክፉና ደጉን የለየ ሰው የሚያስበው ጤነኛ ሃሳብ ነው ማለትስ ይቻላል?

ከእገዳው ባሻገር የሚደንቀው ነገር ደግሞ በፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ላይ የተደረገው ድብደባ ነው። የሆነ ማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ያለ ይመስላል። የጭካኔያቸውን መጠን እንድናውቅ የሚደበድቡት አቅመ-ደካሞችን፣ ሽማግሌዎችንና ሴቶችን እየመረጡ በፍጹም አረመኔነት ነበር። ይህን ተግባራቸውን ስመለከት የደረሱበትን የዝቅጠት ደረጃ መታዘብ ችያለው። ከፖለቲካ ልዩነትም፣ ከአምባገነንነትም በላይ ሰዎቹ እንደታመሙ ነው ለመረዳት የቻልኩት፤ ስር የሰደደ የቁስ ሰቀቀንና የሥልጣን ጥም የተጣባቸው፤ ለዚያ ሲሉም የትኛውንም አይነት ውርደት ለመቀበል የቆረጡና የሞራል ልዕልናቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ሰዎች ናቸው። ስነ-ልቦናቸው ክፉኛ ተቃውሷል እንጂ ሀገር እመራለሁ የሚል ቡድን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈጽማል ለማለት እቸገራለሁ። በአባላቶቻችን ላይ ክፉኛ ድብደባ ተፈጽሟል፤ እስከዛሬም እግሮቻቸው መራመድ የማያስችላቸው፤ የሚያነክሱ ሰዎች አሉ። እውነት ለመናገር ይሄ እብደት ነው። አንዲት እራሷን መከላከል የማትችል ሴትን ለሦስት መደብደብን ከዚህ በተሻለ ልገልጸው አልችልም።

አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር፤ ለኛ ዋናው ጉዳይ የዜጎቹ ሕጋዊነት ወይም ሕጋዊ ያለመሆን ጉዳይ አይደለም። በምንም አይነት መንገድ ሴቶች እየተደፈሩ፤ ወንዶች በየስርቻው እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው እየተገደሉ፤ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ታጉረው ይህን ሁሉ መከራ መቀበላቸውን ልንታገሰው፤ ወይም ከሕጋዊነት አንጻር እየተራቀቅን ልንመለከተው አንችልም። ስለሕግም ከተወራ የሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ጭፍጨፋው ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ላይ ጭምር ሲፈጸም እንደነበር አምኗል።

ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የአንዱ ሀገር ዜጋ ካለ ሀገሩ መገኘት ሀገር ይያዝ የሚያስብል አይደለም። መውጣት ካለባቸው ጊዜ በመስጠት፣ ከመንግሥታቸው ጋር በመነጋገር በዘዴ ነገሩን መከወን እየተቻለ አንድ ሀገርና መንግሥት በሰዎች ላይ እንዲህ የጭካኔ ጥግ የሆነን አቋም ይዘው መንቀሳቀሳቸው ፍጹም ኢ-ሰብዓዊነት ነው።
ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ አስከፊ ጊዜ የለም፣ እውነቱን ለመናገር ለአገዛዙ ሰዎች የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋም አፈር ተደፍቶባታል፣ እንዲህ ግልጽ የሆነ ጭፍጨፋ እየደረሰብን እንኳ በድፍረት ለመናገር አልፈለጉም። ስለኢትዮጵያውያን መገደል ለማውራት ሲፈልጉ ሌላ ሀገር ይጠቅሱና እነሱም እኮ እየተገደሉ ነው ይላሉ፣ ወገን ከምንለው የማኅበረሰባችን አካል ይሄን መስማቱ ከጥቃቱ ይበልጥ ያማል።

ለምሳሌ ኢቲቪ ስጉዳዩ ሲያወራ ሕገ-ወጥ ሊባል የሚችል ድርጊት ተፈጽሟል በማለት ነው። ተመልከቱ! እንዴት ያለ ባዕድነት ነው? ኢትዮጵያውያን በድህነትም ውስጥ እንኳ ለክብራችን የመሞት ባህሪ አለን፣ ይሄ ከቀደሙት አንጡራ ኢትዮጵያውያን የወረስነውና ዛሬም ያለን ሀብታችን ነው።

ትናንት ፍየል ጠባቂ የነበረ በረኸኛ ይህን ክብራችንን ገፍፎ እንደውሻ ቀጥቅጦ ስርቻ ሲጥለን ያልተቆጣ መንግሥት ኢትዮጵያዊ ነው? ከዜጎቹ የወጣና ለህዝቡ የቆመ እውነተኛ መንግሥት ከዚህ የበለጠ የሚቆጣበት ጉዳይ ከወዴት ይመጣል? እውነተኛ መንግሥት ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሳውዲ ካምፓኒዎችን በሰዓታት ውስጥ ማባረር፣ ኢምባሲውን ዘግቶ አምባሳደሩን ማሰናበትን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር። የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነቴ ሊበላሽ ይችላል ብሎ እኛ ድምጻችን እንዳናሰማ ደበደበን፣ አፈነን። በግልጽ እንደሚታየው የጥቅም ትስስሩ ነው አፋቸውን ያዘጋቸው፣ ይህች ጥቅማቸው እንዳትቋረጥ በዜጎች ሕይወት መደራደርን መርጠዋል።

ስነልቦናቸው የተቃወሰ በመሆኑና ተራ ስስታሞች በመሆናቸው እንጂ ኢንቨስትመንትም ሆነ ዲፕሎማሲ ግብአትነታቸው ለሰው ልጅ ነው፣ እንደ አህያ ሲያፈጋ ከርሞ ሬሳቸውን ለላከ መንግሥት እንዴት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመመለስ ይገዳል? እንዴት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታሪካዊትና ለአፍሪካ የነፃነትና የኩራት ተምሳሌት የሆነች ሀገርን እየመሩ እንዴት ትናንት የነዳጅ ዘይት ባቆማቸው እረኞች ስትዋረድ ዝም ይላሉ?!
እንዴት!
በዜጎች ሕይወት የተደራደረው አገዛዝ ማለፉ አይቀርም፣ ለዚህ ጥርጥር የለኝም። ታሪክ ለመጥቀስ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግኝም። የቅርብ የሰሜን አፍሪካ አምባገነኖች የከፋ ፍጻሜ አለና። ኢትዮጵያውያን ፍቅርም ፀብም እናውቃለን፣ ሳውዲዎችም የፈጸሙትን ግፍ ማወራረዳቸው አይቀርም። በዚህ ክፉ ጊዜ ስለሰብዓዊ መብት ቆመናል የሚሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው እውነተኝነታቸውን ለመመርመር ጥሩ ዕድል ይሰጠናል።
መንግሥት ቢኖረን ኖሮ ይሄ ሁሉ ውርደት ይፈጸምብን ነበር ብዬ አላስብም። በዚህ ሰዓት ርዕሰ-መንግሥት ብሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ድርጅት እንደመሆኑ፣ ወደየትኛውም ሀገር የሚደረገውን ጉዞ አቋርጨ ዜጎቼን ማስወጣትን አስቀድም ነበር። ያሄ ጥቂት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊያመጣብን ቢችልም ከከፋው የዜጎች ስቃይ ጋር ግን በአንድ ሚዛን ላይ አይቀመጥም። የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል ድርጅት አለ። በዜጎቻችን ላይ ጎርፍና ድርቅ ሲመጣ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው? ይሄም ሰው ሰራሽ አደጋ ነው፤ ሙሉ ኃይሉን ወደዚህ አዙሮ ሊንቀሳቀስ ይገባው ነበር።

እርግጥ ነው ባቀድነው መሰረት ሰላማዊ ሰልፉ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዳይሆን አድርገውታል። ጩኸቱ ግን ይቀጥላል … ባለን አቅም ሁሉ አፈናውንም፣ ወከባውንም ተቋቁመን ለዜጎቻችንና ለኢትዮጵያዊነት እንታገላለን።

አገዛዙ ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያፍን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድ መልዕክት አስተላልፏል፣ ይህን መልዕክት እንዲያስተላልፍ ማስገደዳችንም ለኛ ትልቅ ስኬት ነው። የሳውዲ መንግሥት ያሻውን ያደርግ ዘንድ የፈቀድኩት እኔ ነኝ፣ በመሆኑም እሱን በመቃወም ግንኙነቴን አታበላሹ ብሎ እርምጃ በመውሰዱ ህዝቡ የነገሩ ቁልፍ የት እንዳለ፣ የአጥቂዎቹ በራስ መተማመን ምን ላይ እንደቆመ በጠራ ሁኔታ ለመመልከት እንዲችል ሆኗል።

ይሄ ሁሉ ነገር እየተፈጸመ የተስተዋለ አንድ ነገር አለ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታ እውነተኛ ማንነታቸው፣ እውነተኛ በአገዛዙ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ያሳየን ክስተት ነው። እንደሚታወቀው እሳቸው በኢህአዲግ እንጂ በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጡ አይደሉም። ኢህአዲግ የሚናገረው ከሌለ እርሳቸው የሚሉት አይኖርም። እንደ አንድ ሀገርና ህዝብ መሪ ግን የመኮነንም ሆነ የማጽናናት ቃል ይጠበቅባቸው ነበር።

ባሉበት ቦታ ያስቀመጣቸው ህወሓት ነው፤ ድርጅቱ ደግሞ ይሄን አቋም አልወሰደም። ስለዚህ እንደሚቆጣቸው ስለሚያውቁ ዝምታን መረጡ፣ ቸልታንም አስበለጡ። በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ በላይ ሽንፈት ያለ አይመስለኝም።


ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

(ይህ ጽሁፍ በፋክት መጽሔት ተስተናግዷል፣ ነገር ግን መጽሔቱ ላልደረሳቸው ሰዎች ይደርስ ዘንድ እዚህ ለማስተናገድ ወደድኩ።



Viewing all articles
Browse latest Browse all 931

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>