አንድ የተረት ምሳሌ ላስነብባችሁ ወደድኩ ሰውየው መልካቸው የጠቆረ ጥርሳቸውም ክፉኛ የገጠጠ ማራኪ ፊት የሌላቸው የመንግስት ባለስልጣን ናቸው፡፡ እናማ በእርምጃ እየለኩ ለገበሬው መሬት ሲያከፋፍሉ ውለው አመሻሽ ላይ ለመጨረሻው ሰው በውሃ የተበላ ቦረቦር መሬት ተራምደው ለኩና ድርሻህ ይሄ ነው አሉት… በዚህ ጊዜ ችግር ገጠማቸው፡፡ ቦረቦር መሬት የደረሰው ገበሬ ዱላ ቀረሽ ሙግት ገጥሞ አሻፈረኝ አለ፡፡
ያን ጊዜ ባለስልጣኑ ሆን ብለው ሳይሆን እድል ፋንታው የጣለለት መሬት እንደሆነ በመግለፅ ምንም ሊረዱት እንደማይችሉ ሲያረጋግጡ በሁኔታው የተበሳጨው ገበሬ ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት አውሬ የመሰልክ ገጣጣ ሲል ባለስልጣኑን ተሳደበ፡፡ ባካባቢው የነበረ ገበሬ ሁሉ ስድቡን ሰምቶ በድንጋጤ ጭብጦ ሲያክል ተሳዳቢው ከአፉ የወጣው ቃል የሚያመጣበትን ውርጅብኝ ለመቀበል ተሰናዳ፡፡ ባለስልጣኑ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱለት “ደግ ሰደብክልኝ ይሔንን ገጣጣ ጥርሴን እኔም አልወደውም ነበር” መልስ ይሏችኋል እንዲህ ነው…..
እናማ አባቶቻችን እንዲህ እየተረቱ አስተምረውን እውነት መስሎን መንግስታችንን ጥርስህ ገጥጧል ብንለው በገባንበት ገብቶ እያሳደደ ጥርሳችንን ለማራገፍ ይጣደፍ ጀመረ፡፡ ወንድም እህቶቻችን በሳውዳረቢያ መንግስት ግፍ ተፈፀመባቸው ብለን ለተቃውሞ ለመውጣት ብንሰናዳ ለዜጋ ሞት የማይገደው መንግስታችን ስብሰባ ላይ ስለሆንኩ ስትጮሁ ትረብሹኛላችሁ ብሎ ከለከለን፡፡
ብርቱ ህዝባዊ አቅም በመገንባት ይህንን አምባገነናዊ ሥርአት ለማስወገድ በአንድነት እንነሳ፤ በተናጥል እየተንጠራወዝን የጥጋበኛ ወታደር መቀለጃ አንሁን ብንል…….የጦርነት አባዜ የተጠናወታቸው፤ ከማይጠቅም ፉከራ በቀር የኢትዮጵያን ፖለቲካ አንድ ስንዝር ሳይገፉ ባህር ማዶ ተቀምጠው በወንጭፍ መምራት የሚፈልጉ ሌላ ፈተና ይደቅኑብን ጀመር፡፡
እጅግ በርካታ ሀገር ወዳድ ዲያስፖራ አጋሮቻችን በገንዘባቸው፤ በእውቀታቸው፤ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ከጎናችን በመቆም ሰላማዊ ትግላችንን ሲደግፉ፤ ጥቂት የጦርነት አባዜ የተጠናወታቸው በዲያስፖለራው ስም በመከለል የሀገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል እንዲኮላሽ ቀን ከሌት እየተጉ መሆናቸው አሳዛኝ ነው፡፡
ላላፉት 22 ዓመታት በአውራ ፓርቲ ስርአት የፖለቲካ ስልጣንን፤ ወታደራዊ ኃይልን፤ መንግስታዊ ተቀዋማትን እና በጠቅላይነት ምጣኔ ሃብትን የተቆጣጠረው ወያኔ መራሹ የኢህአዴግ መንግስት በገነባው ጉልበት የቱንም ያህል ብንቀጠቀጥም ሀገራችንን ለዚህ ጨካጭ ሥርዓት ትተን የትም አንሄድም በማለት ለምናደርገው ትግል ደጋፊ መሆን ሲገባቸው በሰላማዊ ትግል ላይ ተስፋ ቆርጠን እንድንበተን እየጣሩ ነው፡፡
እነዚህ ከሀገር ውጪ ሆነው የሀገር ውስጡን ፖለቲካ እኛ እንምራው ባዮች የተላለኪ ባህሪ ይዘን እነሱ ያሉትን ካላደረግን ሲፈልጉ ፍርሀት ነው፤ ሲያሰኛቸው የአቅም ማጣት ነው ከማለት ተሻግረው፤ የመጨረሻ ፍረጃቸውን ወያኔ ናቸው ወደማለት ያሸጋግሩታል፡፡
ደግሞ ከሰሞኑ አንድነት ፓርቲን በማብጠልጠል ዘመቻ ከፍተን እናዳክም እና የሀገር ውስጡን ፖለቲካ እኛ በተላላኪ እንምራው የሚል አቀቋም የያዙ ኃይሎች ዝግጅት ማጠናቀቃቸው እየተደመጠ ነው፡፡ ይህ ዘመቻ ከቀጠለ ከሀገር ውጪ ሆነው ጦርነት የመረጡ፤ ሀገር ውስጥ ካሉ ፓርቲን ባይወክሉም የፓርቲ ፊት አውራሪ ነን ከሚሉ ጋር የተደረገውን ዱለታ የሚያረጋግጥ መረጃ ይፋ ለማድረግ ግድ ይሆናል፡፡
Related articles
- ርዕዮትና እስክንድር የኢትዮጵያን መንግስት በአፍሪካ ህብረት ፍርድ ቤት ሊሞግቱት ነው፡፡Ethiopian Journalists Challenge Anti-Terrorism Law (asefatesfaye.wordpress.com)
- አቶ ሽመልስ ከማል ‹‹ የሳውዲ መንግስት ሉአላዊ መብት አለው›› (dawitfw.wordpress.com)
