የተከበራችሁ የዲሲ እና አካባቢው ነዋሪዎችዛሬ ለዚህ መድረክ የማስተላልፈውን መልዕክት ከምን እንደምጀምር ሳስብ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መርዕ የተጀመረውን ህዝባዊ መነሳሳት መፍጠሪያ መድረክ እንደሚሆን ጥርጥር አልነበረኝም፤ ነገር ግን ሀገር ውስጥ በሚታተም አንድ መፅሄት ላይ ወጥቶ ለንባብ የበቃውን የአንዱዓለም አረጋጌን “የሐምሌ ጨረቃ”.. መጣጥፍ ሳነብና የእርሱን የሰለማዊነት መንፈስ ለገዥዎቻችን ግን የአሸባሪነት ድምፅ ትንሽ ማለት እንዳለብኝ ተሰምቶኛል፡፡ የአንዱዓለም መዝሙር የእኛም መዝሙር ስለሆነ፡፡ በገዢው ፓርቲ እና በእኛ በኩል ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የመደማመጥ ችግር እንዳለም ማሳየ ነው፡፡ ሰለ ሰላም የሚዘምርን ሰው አሽባሪ ለማለት ያለ የሌለ ጉልበታቸውን ያባክናሉ፡፡
በቅርቡ ብዙዎቻችሁ በሚዲያ እንዳያችሁት “የፀረ አሸባሪነት ህግና የፓርቲዎች አቋም” በሚል ርዕስ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ ውይይት በእኛ እምነት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የሚለው ዘመቻ ካሰገኛቸው ውጤቶች አንዱ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በ2001 የፀደቀን አዋጅ እንደገና ወደ መድረክ ማምጣ መቻል ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ የቴሌቪዥን ውይይት ተቆርጦ ተቀጥሎ የቀረበ ቢሆንም አንድነት ነጥብ አስቆጥሮ የወጣበት ነው፣ በዚህ ውይይት የፀረ አሸባሪነት ህጉ ዜጎችን ከአሸባሪ ጥቃት ለመታደግ ሳይሆን ኢህአዴግ ድምቸውን የሚያሰሙ ዜጎችን ማፈኛ እና ሲከፋም ህዝቡን የሚያሸብርበት እንደሆነ ለህዝብ ይፋ ተደርጎዋል፡፡
ከህዝብ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩ ሚዲያዎች የአንድ ፓርቲ ወገንተኛ ሆነው ሲያገለግሉ ማየት በሀገራችን ኢትዮጵያ መደብኛ እና ትክክል እስኪመስል ድረስ የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኖዋል፡፡ እዚህ ማንሳት የፈለኩት በሚዲያ የተላለፈው ዝግጅት የእነ አንዱዓለምና እስክንድር እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካና የእሊና እስረኞች ስም የተነሳበት ቦታ በሙሉ ከተቆረጠና ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ኢህአዴግ አንዱዓለምን ውጭ ሆኖ ሲታጋል ሳይሆን በሚዲያም ሰሙ ሲጠራ ይፈራል ማለት ነው፡፡ የአንዱዓለም እስር በምንም ዓይነት ከአሸባሪነት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ስለሚያውቁ ሰማቸው ሲነሳ መንፈሳቸው ይረበሻል፡፡ በፈንጂ የሞቱ ሰዎችን ፊልም እያሳዩ፣ በአሸባሪነት የከሰሱና እሰከ እድሜ ልክ እስር የፈረዱባቸው አንዱዓለም እና እስክንድር ግን ብዕር ይዘው ነው የታሰሩት፡፡
አንዱዓለም የታሰረው ሹሞች በሁለት ሺ ሁለት ምርጫ በያዙበት ቂም ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ አንዱዓለም ግን በተቃራኒው እስር ቤት የወረወሩትን ሰዎች በፍቅር ለማሸነፍ እንደሚቻል ከእስር ቤት ሆኖ ሰለ ሰላም ይሰብካል፡፡ በተቃራኒው የኢህአዴግ ሹሞች ሰለ እነ አንዱዓለምና እስክንድር መናገር አሸባሪነትን በተዘዋዋሪ ድጋፍ እንደማድረግ ነው በሚል አንገታችንን ሊያስደፉን ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ እኛም የአንዱዓለምን የሰላማዊ ትግል መንፈስና ጥንካሬ ሊኖረን እንደሚገባ አሰረግጨ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ሰለማዊ ትግል የሚሞትለት እንጂ ግዳይ ተጥሎ የሚፎከርለት አይደለም፡፡ የምንሞትለት እንጂ የምንገልበት አንድም በቂ ምክንያት አይኖረንም የለንምም፡፡ የሰላማዊ ትግል ጀግንነት ለሞት ጭምር ደፍሮ ለመግደል ፈሪ መሆንን ነው፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ዘመቻ ይህን ሰላማዊ ትግል ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ መሰረት የሚጣልበት ይሆናል ብለን አምነን ነው የተነሳነው፡፡ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት አይጋ ፎረም እና ደጋፊዎቹ እንደሚሉት ሚሊዮን ፊርማ አሰባሰቦ የፀረ አሸባሪነት ህግ እንዲሰረዝ ግፊት ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ሚሊዮኖች ነፃ መሆናቸውን የሚያሳዩበት የህዝብ ንቅናቄ ነው ፣ ይህ ለሁላችን ግልፅ እንዲሆን በአጭሩ ላስረዳ፤
• ሚሊዮኖች ፊርማቸውን በግልፅ በማኖር ከፍርኃት ነፃ መሆናቸውን ያሳያሉ፤
• ሚሊዮኖች ህዝባዊ ስብሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ በመሳተፍ ድምቸውን
• ሚሊዮኖች ይህን እንቅስቃሴ ፋይናንሰ በማድረግ በገንዘብ ወይም በእውቀታቸው እና በጉልበታቸው ይሳተፋሉ
• በመግቢያ እንዳነሳሁት በፀረ አሸባሪ ህግ ሰለባ የሆኑትን ታሳሪዎች በግንባር ተገኝቶ መጠየቅ ማበረታት
• ቤተሰቦቻቸውን በሁሉም መልኩ መደገፍ የነፃነት መገለጫ ነው፡፡
እነዚህን ማስፈራሪያዎች በጣጥሶ ወጥቶ የነፃነት ጌታ መሆን ያሰፈልጋ፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ደፍሮ ማድረግ የቻለ አንድ ኢትዮጵያዊ መብቱ ሲነካ እንቢ በቃኝ ለማለት ድፍረት ያገኛል የሚል እምነት አለን፡፡ ሚሊዮኖች በአንድ ወይም በሌላው ለነፃነታቸው መቆማቸው ገዢዎች በፍርሃት ቆፈን ውስጥ አድርገው የሚገዙበት ሁኔታ እንዲያበቃ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ለነፃነት ለሚደረገው ትግልም በቂ የሰው ሀይል እና በማቴሪያል ለማሰባሰብ እና ትግሉን ወደፊት ለመምራት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ሰላማዊ ትግል ለምን ውጤት አላመጣም ለሚለው ጥያቄ የሰላማዊ ትግል የገባው ሰራዊት ማፍራት ያለመቻላችን ዋነኛው መንስዔ ሲሆን የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ለዚህ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል የሚል ተሰፋ ሰንቀን ነው የጀመርነው፡፡ ዛሬ በዚህ ቤት የተገኛችሁ ሁሉ ይህን ድምፅ ተቀላቅላችሁዋል ብዬ መውሰድ እችላለሁ፡፡ በተለምዶ ከምናውቀው የጦርና ጎራዴ፤ የፈረስና ታንክ፣ ጅግንነት ወደ የሰላመዊ ትግል ጀግንነት ልዕልና ልናሳድገው ይገባል፡፡ ለእኛ እን አንዱዓለም ናትናኤልና እስክንድር የሰላማዊ ትግል ጀግኖቻችን ናቸው፡፡ ዛሬም በወህኒ ቤት ሆነው ብዕራቸው ፍቅርና ሰላምን ይሰብካል፡፡ በቀልን ያወግዛል፡፡ የሰላማዊ ትግል ጀግንነት የሚወዱህን በመውደድ ሳይሆን የሚጠሉህን ጨቋኞች ለሰላም እጃቸውን እንዲዘረጉ ሰላማዊ በመሆን ነው፡፡
የዛሬ አራት ወር አካባቢ በዲሲ ተገኝቼ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅሰቃሴ ብዙ እንደምንማር ነግሬያችሁ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ አሁንም ብዙ የምንማረው ነገር ቢኖርም እሰከ አሁን ባደረግነው እንቅስቃሴ ሰላማዊ አድርገን እንቅስቃሴያችንን ለመምራት የቻልነው ግርግር ሳንፈጥር መልዕክት ማሰተላለፍ እንደምንችል ለደጋፊዎቻችን እንደምሳሌ በማሳየት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም መዋቅራችን አስፍተን መስራትና ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል ለመድረስ የምንችለውን ለማድረግ በቁርጠኝነት በመስራታችን ነው፡፡ ይህ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት በስትራቴጅክ እቅድ በተቀመጠቅ መሰረት ዘላቂነት ያለው መዋቅር ለመግንባት ባደረግነው እንቅስቃሴ የተገኘ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሙስሊሞች በፖለቲካው ተሳትፎ ከዚህ በፊቱ በላቀ ሁኔታ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ይህ ግን ገዢውን ፓርቲ አላስደሰተውም፡፡ ያስደስተዋል ተብሎች አይጠበቅም፡፡ ለዚህም ነው ዘወትር እምነትና ፖለቲካ ቀላቀላችሁ እያለ ፕሮፓጋንዳ የሚነዛው፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ዘመቻ እንደሚታወቀው በመስከረም 5 በሚደረግ የአደባባይ ስብሰባ እንደሚጠናቀቅ እና ከዚህ እንቅስቃሴ በተገኘው ተሞክሮ በመነሳት ሌላ ዕቅድ የሚወጣ ሲሆን በሁሉም መመዛኛ እሰከ ዛሬ የተደረገው እንቅስቃሴ ግን በሀገር ውስጥ የተንሰራፋውን ልክ ያጣ ፍርሃት ድባብ ለመግፈፍ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ለዚህም በሁሉም መስክ ድጋፍ ያደረጋችሁ ሁሉ ልትኮሩ ይገባችሁዋል፡፡ ወደፊትም በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያ የአቅማችሁን በማድረግ ትግሉን ማገዝ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ማስገደጃውም አብሮን ያለው የህሊና ፍርድ ነው፡፡ ከሃላፊነት ለመሸሽ ምንም ዓይነት ሰበብ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው አምባገነን ሰርዓት እንዲወገድ ፍላጎት ያለን ሁሉ ማድረግ ያለብን ከፍርሃት የተላቀቀ ዜጋ ከማበርከት ጎን ለጎን በድፍረት ወንጀልን ከመስራት የሚቆጠብም ጭምር እንዲሆን በማድረግ ነው፡፡ የወንጅል ስር የሚጀምረው ደግሞ ከመጠላላት፣ ከቂምና በቀል ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት አርባ ዓመታት ለለውጥ ፍላጎት ያላቸው ልጆቿ በተለያየ ጎራ ተሰልፈው መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ከመስዋዕትነት የተረፉት አሁን በተለያየ ጎራ ተሰልፈው ይገኛሉ፡፡ አሁንም በውል ያልተቋጨ የእርስ በእርስ ያለመተማመን፣ መፈራትና የአሸናፊነትና የተሸናፊነት ሰነ ልቦናዎች በፖለቲካው ሜዳ ላይ ገዢ ሆነው ይታያሉ፡፡ እነዚህን ወደ ጎን ትተን ሀገራዊ መግባባት የምንፈጥርበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው በመከበባር እና ተቀራርቦ በመነጋገር እንጂ በመናናቅ እና በስድብ ሊሆን አይችልም፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የመሳሪያ ሀይልን የጉዳይ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጎ መውሰድ በየትኛውም መመዘኛ ጠቃሚ አይደለም፡፡
Related articles
- እስክንድር ነጋ በኢትዮጲያ ላይ የኢኮኖሚ ተፅእኖ እንዲደረግና ግፍ በፈፀሙ ባለስልጣናት ላይ ጉዞ እገዳ ጠየቀ (daniboy8935.wordpress.com)
- እስክንድር ነጋ በኢትዮጲያ ላይ የኢኮኖሚ ተፅእኖ እንዲደረግና ግፍ በፈፀሙ ባለስልጣናት ላይ ጉዞ እገዳ ጠየቀ (addisuwond.wordpress.com)
- አዛውንቷ፣ ሾላውና ዋርካው (The Elderly Lady and Two Trees) (kweschn.wordpress.com)
