‹‹ሼሕ ኑሩን ማን ገደላቸው?›› በሚል ርዕስ በመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተሰናድቶ ነሐሴ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት በቀረበው ዶክመንተሪ ላይ… በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመንና በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲን ተቀባይነት ለመሻር በማሰብ ስሙን ማጥፋት ወንጀል መሆኑን፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ገለጸ፡፡
‹‹የሙስሊሞችን ጥያቄና የሼሕ ኑሩን ግድያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ማያያዝ ወንጀል ነው፤›› በማለት ፓርቲው ባስተላለፈው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ዶክመንተሪው የገዢውን ፓርቲ ብፅዕና ከመተረክም በላይ፣ ፍረጃንና ጉልበተኝነትን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ከአኬልዳማና ከጅሀዳዊ ሐረካት የቀጠለ በፓርቲውና በዜጎች ላይ የተቃጣ ሕገወጥ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ገልጿል፡፡
የመንግሥትነት ሥልጣን የያዘ ፓርቲ አገራዊ ችግሮችን ለምን በዶክመንተሪ ፊልም ለመፍታትና ለማዳፈን እንደሚጥር እንቆቅልሽ እንደሚሆንበት የገለጸው አንድነት ፓርቲ፣ ከዜጎች የሚነሱ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንዳለባቸው ፅኑ እምነቱ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሙስሊሞች ጥያቄ በውይይትና በመግባባት ላይ ተመሥርቶ ሊመለስ እንደሚገባና የኃይል ዕርምጃውም መቆም እንዳለበት አንድነት አክሏል፡፡
‹‹መንግሥት ሕዝቡን በዶክመንተሪ ፊልም በማስፈራራት ለማሳመን ከመድከም ባሻገር፣ ዴሞክራሲያዊ ባህሪን መላበስ አልተቻለውም፤›› የሚለው አንድነት ፓርቲ፣ ዶክመንተሪ ፊልሙ የፍረጃ ፖለቲካ የተንፀባረቀበት፣ የተለየ ሐሳብና ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦችንና ተቋማትን የማሸማቀቅና የማጥፋት እኩይ ተግባር ማሳያ መሆኑን በመግለጫው አብራርቷል፡፡
የኢሕአዴግ የጉልበት አካሄድ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣን አባብሶ ከመቀጠል ውጭ መፍትሔ የማያመጣ መሆኑን የገለጸው አንድነት ፓርቲ፣ የአንድነትን ሰላማዊ ትግል ሊቀለብሰው እንደማይችልም አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤት በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ አድርጎ ውሳኔ ሳያሳልፍ በቴሌቪዢን ፍርድ መስጠቱ፣ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሕግ የማይገዛ አምባገነን ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያና የፍትሕ ሥርዓቱ ልዕልና እየተገፋ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቁሟል፡፡
‹‹የሙስሊም ወንድሞቻችን ሁለት ዓመት የዘለቀ ጥያቄና የሼሕ ኑሩን ግድያ ከአንድነት ፓርቲ ጋር በማያያዝ፣ ፖለቲካዊ ጥያቄ ለማስመሰል መሞከር ጥፋትም ወንጀልም ነው፤›› የሚለው አንድነት ፓርቲው ዘር፣ ፆታ፣ ሃይማኖትና ቀለም ሳይለይ ዜጎች የሚያነሱትን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እንዲመልስ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ማግባቱን እንዲያቆም ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የ33ቱ ፓርቲዎች ትብብር ባወጣው መግለጫ፣ ነሐሴ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢድ አልፈጥር በዓል ቀን መንግሥት በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሰላማዊ ትግል ላይ የወሰደውን ዕርምጃ እንደሚያወግዝ ገልጿል፡፡
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠለትን የዕምነት ነፃነት መብቱን በተመለከተ ‹‹ጣልቃ አትግቡብን›› ሲል ያቀረባቸውን ሦስት ጥያቄዎች፣ መንግሥት በሠለጠነ መንገድ በውይይት መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ ተወሰደ ያለውን ሕገወጥ ዕርምጃ ትብብሩ እንደሚያወግዝ ገልጿል፡፡ መንግሥት ከሕገወጥ ዕርምጃና ፍረጃ እንዲቆጠብ፣ በፈጠራ የሽብር ወንጀል ያሠራቸውን የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እንዲፈታና ለጥያቄያቸውም ፍትሐዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄውን በድጋሚ አቅርቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ‹‹ጽንፈኞች›› ካሉዋቸው ጋር በመሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገር ለመበጥበጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በመግለጽ፣ ፓርቲዎቹን ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
Related articles
- የግዕዝ ፊደል ስረ፥መሰረት – Origins and Usage of Ge’ez (leaimerom.wordpress.com)
- Ethiopian Muslims protest on Eid holiday | The Stream – Al Jazeera English (sileshihagos.wordpress.com)
